ወጥ የሆነ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ አለመኖሩ ጉዳት ማስከተሉን ጥናት አመለከተ

መጋቢት 09/2013 (ዋልታ) – በኢትዮጵያ ራሱን የቻለ ሀገር አቀፍ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ አለመኖሩ በግብርና ስራ፣ በምግብ ዋስትና በምርታማነት እና ተያያዥ ጉዳዮች ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ በዘርፉ የተካሄደ ጥናት አመለከተ፡፡

“የኢትዮጵያ የመሬት ፖሊሲ ዝግጅትና አተገባበር” በሚል ርዕስ ላንድ ፎር ላይፍ ኢትዮጵያ ያሰራው ጥናት እንዳመለከተው፣ ባለፉት የመንግስት ስርዓቶች በተሰሩ የፖሊሲ ስሪቶች ከፖሊሲ አወጣጥ ጀምሮ በአተገባበርና በአፈጻጸም ክፍተት ያለበት ሆኖ ተገኝቷል፡፡

የጥናት ቡድን መሪ የሆኑትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአገር ልማት ኮሌጅ መምህር ዶክተር መሳይ ሙሉጌታ የፖሊሲ ስሪቱ የተማከለ እንደነበር፣ ህብረተሰብን በበቂ ሁኔታ ያላሳተፈ፣ ህዝብን ያላማከለ፣ ህጎቹ የተበታተኑና ለአተገባበር የማይመቹ ሆነው በጥናቱ መለየቱን አመልክተዋል፡፡ በመሆኑም ወጥ የሆነ የመሬት ፖሊሲ እንደሚያስፈልግ ነው የጠቆሙት፡፡

በርካታ ፖሊሲዎች፣ አዋጆችና እስትራቴጂ ሰነዶች እያሉ እስካሁን ድረስ የአካባቢ ጉዳይ፣ የምግብ ዋስትና፣ የእርሻ ስራና ምርታማነት አስቸጋሪ ሆኖ የቀጠለው አሰራሩ የህዝብን ችግር ግምት ውስጥ ያላስገባ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ራሱን ችሎ የተዘጋጀ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ እንደሌለና የመሬት ፖሊሲው የሚገኘው ተበታትኖ በተለያየ ቦታ መሆኑን ገልጸው፣ ህጎቹ የሚገኙት በተበታተነ መንገድ በአዋጆች፣ በህገ መንግስቱ፣ በፕሮግራምና በተለያየ አንቀጾች ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም ራሱን የቻለ “የኢትዮጵያ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ ሰነድ ያስፈልጋል” ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡