ግብጽና ሱዳን የህዳሴ ግድብን ለውስጥ የፖለቲካ ችግሮቻቸው መፍትሄ ለማድረግ እየጣሩ ነው – ምሁራን

መጋቢት 09/2013 (ዋልታ) – ግብጽና ሱዳን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን የውስጥ ፖለቲካ ችግሮቻቸው የመፍትሄ ቁልፍና ማረጋጊያ ለማድርግ እየጣሩ መሆኑን ምሁራን ተናገሩ።

ኢትዮጵያዊያን የግድቡን ግንባታ በፍጥነት በማጠናቀቅ አገር ወዳድነታቸውን በተግባር ማሳየት እንደሚገባቸውም ተጠቁሟል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የዲፕሎማሲና የታሪክ ምሁራን እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የተሻለ የተፈጥሮ ሃብት ቢኖራትም ሃብቱን እስካሁን ጥቅም ላይ ባለማዋሏ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ በድህነትና በኋላቀርነት እንድትነሳ አድርጓታል።

ኢትዮጵያ የውሃ ሃብቷን ጥቅም ላይ ማዋል ባለመቻሏ የበይ ተመልካች ሆና መቆየቷን ምሁራኑ አንስተዋል።

የጥቁር አባይ መነሻና የአባይን 86 በመቶ ውሃ አመንጪ የሆነችው ኢትዮጵያ ብትሆንም ወንዙ ድንበር ተሻግሮ የግብጽና ሱዳንን የኤሌክትሪክ ሃይልና የእርሻ ፍላጎት ሲያሟላ ለዘመናት ቆይቷል።

በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1929 እንዲሁም በ1959 ግብጽና ሱዳን ውሃውን በብቸኝነት መጠቀም የሚያስችላቸውን የቅኝ ግዛት ስምምነት አድርገዋል።

ሁሉቱ አገሮች አሁንም ድረስ ይህ ውል ተግባራዊ እንዲሆንና ኢትዮጵያ የአባይ ውሃን ተጠቅማ ምንም አይነት የልማት ስራዎችን እንዳታከናውን ያላቸውን ፍላጎት በግልጽ እያሳዩ ይገኛሉ።

ለአብነትም ግብጻውያን በአለም አቀፍ ተቋማት የሚሰሩ ባለሙያዎቻቸውን በመጠቀም ኢትዮጵያ የአባይ ውሃን ተጠቅማ ማንኛውንም መሰረተ ልማት ማከናወን የሚያስችላትን የገንዘብ ድጋፍ እንዳታገኝ ብዙ ሰርተዋል።

የዲፕሎማሲና አለምአቀፍ ግንኙነት መምህሩ እንዳለ ንጉሴ እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ የያዘችው የፍትሃዊ ተጠቃሚነት መርህ በግብጽና ሱዳን ዘንድ ተቀባይነት ያላገኘበት ዋነኛ ምክንያት አገሮቹ የቅኝ ግዛት አመለካከታቸው ባለመቀየሩ ነው።

አገሮቹ ከአፍሪካ አልፎ የተለያዩ አለም አገሮች ጉዳዩን ወስደው መፍትኤ ፍለጋ የመኳተናቸው ምክንያትም የአስተሳሰባቸው ውጤት መሆኑም እንዲሁ።

እኤአ በ2015 ሶስቱ አገሮች በመሪዎቻቸው በኩል ከተፈረመ ስምምነት ውጭ ኢትዮጵያ በአባይ ውሃ ጉዳይ ምንም አይነት ውል እንዳልፈረመች ምሁራኑ ገልጸው፤ “በዚህ ስምምነት አገሪቷ በተፈጥሮ ሃብቷ መልማት እንደምትችል ግብጽና ሱዳን ዕውቅና ሰጥተዋል” ብለዋል።

የታሪክ ተመራማሪና መምህሩ ዶክተር አልማው ክፍሌ፤ የህዳሴ ግድቡ ግንባታ ከዲዛይኑ ጀምሮ እስከ ገንዘብ ምንጩ በኢትዮጵያዊያን መከወኑ የአሁኑ ትውልድ የቀደምት ስልጣኔ ባለቤትነቱን ያስቀጠለበት መሆኑን ማሳያ ነው።

ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ ከጀመረች ጀምሮ በግብጽና በሱዳን ይደርስባት የነበረውን ጫና ተቋቁማ በተፈጥሮ ሃብቷ መጠቀም እንደምትችል የመጀመሪያውን ውሃ መሙላቷ በቂ ማሳያ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ አቋም ከአፍሪካውያን አልፎ ለአለም ትልቅ ትምህርት የሰጠና ለአፍሪካዊያን ይሰጥ የነበረውን የተሳሳተ አመለካከት የቀየረ መሆኑንም ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና ኦሬንታል ጥናትና ምርምር ተቋም መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ በበኩላቸው ግብጽና ሱዳን የአባይ ውሃን የልማት ሳይሆን የፖለቲካ ጉዳይ በማድረግ አለምአቀፋዊ ትኩረት ለመሳብ እየሞከሩ ነው።

“ይሁንና ኢትዮጵያ ላይ ጫና በመፍጠር የአባይ ውሃን ተጠቅማ የመልማት መብቷን የመንፈግ ምኞታቸው አይሳካም” ብለዋል።

ኢትዮጰያ፣ ግብጽና ሱዳን በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት የሚያደርጉትን የሶስትዮሽ ድርድር መቋጫው አፍሪካ ህብረት መሆኑንም ገልጸዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል በግድቡ ጉዳይ ለረጅም ዓመታት ሲደራደሩ የነበሩት አምባሳደር ኢብራሂም እድሪስና ዶክተር አልማው ክፍሌ እንደሚሉት፤ ግብጽም ሆነች ሱዳን የግድቡን ጉዳይ የውስጥ ፖለቲካ ችግሮቻቸውን ለማረጋጋት እየተጠቀሙበት ነው።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ የፕሮጀክቱ መጠናቀቅ የልማት ጥያቄውን ለመመለስ ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን በመረዳት ከልዩነት ይልቅ አንድነትን በማጠናከር የግድቡን ግንባታ ከዳር በማድረስ ሃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ለግድቡ ግንባታ ሁሉም ኢትዮጵያውያን እንደተሳተፉበት ጠቅሰው፤ አጠቃላይ የግንባታው ሂደት 79 በመቶ የደረሰውን ግድብ ቀሪ ስራዎች ለማጠናቀቅ እያንዳንዱ ዜጋ የሚያደርገውን ተሳትፎ በማጠናከር አገር ወዳድነቱን በተግባር እንዲያሳይ ምሁራኑ ጥሪ አቅርበዋል።