ዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ግዙፍ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ሊያስገነባ ነው

ነሐሴ 5/2015 (አዲስ ዋልታ) ዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ግዙፍ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ሊያስገነባ ነው፡፡

ኮርፖሬቱ አሁን ላይ ሁለንተናዊ የለውጥ ስራዎች እያከናወነ ሲሆን በዋናነት አዳዲስ ይዘቶችን በመቅረፅ ለህዝብ ተደራሽ ማድረግ ጀምሯል፡፡

በለውጥ ስራዎቹም በአዲስ ዋልታ ቴሌቪዥን አዲስ መንገድ በመጀመር ለአድማጭ ተመልካቾች እያቀረበ የሚገኝ ሲሆን ይህንንም ውጤታማ ለማድረግ ኮርፖሬቱ የራሱ የሆነ ግዙፍ የሚዲያ ኮምፕሌከስ ለመገንባት ዝግጅት እያረገ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

የኮርፖሬት የስራ አመራር ቦርድ አመራሮች እና የኮርፖሬት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት እያካሄደ ባለው መዋቅራዊ ለውጥና የሪፎርም ስራ እንዲሁም በቅርቡ ለሚያስገነባው ግዙፍ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ህንፃ ዲዛይን ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡

የተቋሙ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ተስፋዬ በልጅጌ ኮርፖሬት በሚዲያው ዘርፍ ያለውን ተወዳዳሪነት አስጠብቆ ለመሄድ እንዲሁም ተመራጭ ለመሆን እያካሄደ ያለው መዋቅራዊ ለውጥና የሪሮርም ስራዎች የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ ለማስገንባት ያሰበው ግዙፍ የሚዲያ ኮምፕሌክስም ዋልታን ግዙፍ የህንፃ ባለቤት እንዲሆን ከማድረግ ባለፈ ከሀገር አልፎ በአፍሪካ ተወዳዳሪ የሆነ መገናኛ ብዙኃን እንዲፈጠር ያስችላል ብለዋል፡፡

በሳራ ስዩም