የዋልታ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ኮርፖሬት ከዚህ ቀደም ይጠቀምበት የነበረውን የፌስቡክ ገፁን ስያሜ ቀየረ

የዋልታ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ ንጉሴ መሸሻ (ዶ/ር)
የዋልታ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ ንጉሴ መሸሻ (ዶ/ር)

የካቲት 21/2014 (ዋልታ) – ዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ከዚህ ቀደም ይጠቀምበት የነበረውን waltainfo.com የተሰኘ የፌስቡክ ገጽ ስያሜ ወደ WMCC (Walta Media and Communication Corporate) መቀየሩን አስታውቋል፡፡

ከጥቂት ሳምንታት በፊት በመንታፊዎች ተጠልፎ የነበረውን የፌስቡክ ገፅ ከተለያዩ አካላት ጋር በጋራ በመሆን ማስመለስ በመቻሉ ገፁ ወደ ስራ መመለሱን የዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ  ንጉሴ መሸሻ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም waltainfo.com በመባል የሚታወቀው የፌስቡክ ገፅ በመረጃ መንታፊዎች ቁጥጥር ስር በመዋሉ ችግሩ እስኪቀረፍ ድረስ መረጃ ከማጋራት እንደሚቆጠብ መገለፁ ይታወሳል፡፡

በወቅቱም ሊተላለፉ የሚችሉ መልዕክቶች የተቋሙን አቋም የሚገልጽ አለመሆኑን ለፌስቡክ ተከታዮቹ ማሳወቁን የሚያነሱት ዋና ስራ አስፈፃሚው የፌስቡክ ገፁ እስኪመለስ በትዕግስት ሲጠባበቁ ለነበሩ ተከታዮች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ገፁ እንዲመለስ የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን መረብ አስተዳደርና አፍሪካ ውስጥ የሚገኘው የፌስቡክ ኩባንያ አስተዋፅኦ ያደረጉ መሆናቸውን ዋና ስራ አስፈፃሚው አንስተዋል፡፡

በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ የሚደረግ ህገ-ወጥ ተግባራትንና የሳይበር ጥቃት ለመመከት ዋልታ ሚዲና ኮሙኑኬሽን ኮርፖሬት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም ዋና ስራ አስፈፃሚው ገልፀዋል፡፡

ዋልታ በፌስ ቡክ ገፁ ለተከታዮቹ ከዚህ ቀደም ከነበረው በላቀ መልኩ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ እንደሚያደርስ አስታውቀዋል፡፡