ነሀሴ 17/2013 (ዋልታ) – የዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ሰራተኛ ሀምሳ አለቃ ግርማ ባይኔአየሁ ሀገራዊ የክተት ጥሪን በመቀበል የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ለመቀላቀል ሽኝት የተደረገላቸው የተቋሙ የመጀመሪያ ባልደረባ ሆኑ ፡፡
ሀምሳ አለቃ ግርማ ባይኔአየሁ በሽኝት ፕሮግራሙ ላይ ባደረጉት ንግግር ከሀገር በላይ ምንም እንደሌለ ገልጸው ሀገር ችግር በገጠማት ጊዜ መዝመት በመቻላቸው ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል፡፡
የዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ንጉሴ መሸሻ የሀገር ሉዓላዊነት፣ ነጻነት እና ህልውና የሚገዳደሩ ችግሮች ሲያጋጥሙ ኢትዮጵያውያን ዘር ሀይማኖት ጎሳ ሳይለያቸው በአንድነት በመቆማቸው ያሁኑ ትውልድ ለሺህ አመታት ታፍራና ተከብራ የቆየች ሀገር ከአያት ቅድማያቶቹ ለመረከብ ችሏል ብለዋል፡፡
“ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ዛሬ ላይ እንደ ሀገር የገጠመንን የህልውና አዳጋ ቀደምት አባቶቻችን እንዳደረጉት ሁሉ በአንደነት በመቆምና በመተባበር ታሪክ መስራት ይጠበቅበታል” ብለዋል፡፡
ከሀያ አመታት በላይ የመከላከያ ሰራዊት አባል የነበሩት የዋልታ ሰራተኛ መንግስቱ ነጋሽ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በታሪኳ ብዙ ፈተና ገጥማት እንደነበር አስታውስው ዜጎቿ በህብረት በመቆማቸው ሀገሪቱ የተቃጣባትን የታሪክ ሳንካ ሁሉ መሻገር መቿሏን መስክረዋል፡፡
“እቀድማለሁ ተከተለኝ፤ እዘምታለሁ ደጀን ሁነኝ” በሚል መሪ ቃል ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሀገራዊ ሀላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘማቹ ከዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ለስንቅ የሚሆን ድጋፍ የተደረገላቸው ሲሆን የወር ደመወዛቸውም ለቤተሰቦቻቸው እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡