መጋቢት 30/2013 (ዋልታ) – አለም አቀፍ የመምህራን ቀን ማጠቃለያ ክብረ በዓል በአዲስ አበባ ከተማ በመካሔድ ላይ ይገኛል።
በዓሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከበረው ለመምህራኑ እውቅና እና ሽልማት በማበርከት ነው።
በዚህም 143 ለሚሆኑ መምህራን እውቅና እና ሽልማት ይሠጣቸዋል።
በስነስርዓቱ ከሁሉም ክልሎች የተወጣጡ ነባር አንጋፋ እና አዳዲስ መምህራን የታደሙ ሲሆን የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች በተገኙበት እየተካሔደ ይገኛል።
የትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ የመምህርነት ሙያ የተከበረ የራሳቸውን ኑሮ ሳይቀይሩ የበርካታ ተማሪዎቻቸውን ኑሮ ቀይረው ለትልቅ ደረጃ የሚያደርሱ በመሆኑ መምህራን ሊከበሩ እና እውቅና ሊሠጣቸው ይገባል ያሉ ሲሆን በዘላቂነት ይህ እንደሚደረግም ቃል ገብተዋል።
በአሁን ወቅት በሀገር አቀፍ ደረጃ 700ሺህ መምህራን የሚገኙ ቢሆንም በየጊዜው እየጨመረ ከመጣው የትምህርት ቤቶች እና የተማሪዎች ቁጥር ጋር የመምህራኑን ቁጥር ለመጨመር 11ብቻ የነበሩ የመምህራን ማሠልጠኛ ኮሌጆችን ወደ 40 ከፍ ያለበት ሁኔታ ቢኖርም በቀጣይም ተጠናክሮ ይሠራል ብለዋል ሚኒስትሩ።
በአለም አቀፍ ደረጃ በተከሠተው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት 1.8 ቢሊየን ተማሪዎች ትምህርት አቋርጠው በነበረ ጊዜ መምህራን በቁርጠኝነት ያሣዩት ተግባር ሁሉንም መምህራን ሊያስመሠግን ይገባል ሲሉ ሚኒስትሩ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዮሐንስ በንቲ በበኩላቸው የመምህራን ቀን በተለያዩ የክልል ከተሞች ሲከበር ቆይቶ ዛሬ በድምቀት ከፍተኛ የመንግስት ሀላፊዎች በተገኙበት መከበሩ ለመምህራኑ ልዩ ስሜትን የሚፈጥር በመሆኑ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
መምህራን መልካም አስተዳደርን እና ሠላምን ስለሚፈልጉ አለመግባባቶችን በንግግር በመፍታት የመንግስት አካላት ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ የመምህራኑ ጥያቄ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ አንስተዋል።
በመድረኩ የተከበረን ማክበር በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ በትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ገረመው ሉቃ ቀርቧል።
(በድልአብ ለማ)