ዓድዋ የቀኝ አገዛዝ ማዕበልን የገታ ድል

ዓድዋ የቀኝ አገዛዝ ማዕበልን የገታ ድል

በአሳየኛቸው ክፍሌ

ኢትዮጵያውያን ለረጅም ዓመታት ነፃነታቸውን አስከብረው የቆዩ ገናና ህዝቦች ናቸው፡፡ ይህ ነፃነታቸው ግን እንዲሁ እንደዋዛ የተገኘ አይደለም፤ በታላቅ መሰዋትነት የተገኘ በደም እና አጥንት የተዋጀ እንጂ፡፡

ኢትዮጵያውያን ዳር ድንበራቸውን ለማስከበር ነፃነታቸውን ለማስቀጠል ከዓደዋው ድል በፊት በበርካታ አውደ ውጊያዎች ላይ ለሀገራቸው ተፋልመዋል፤ ከመቅደላ እስከ መተማ፣ ከጉራ እስከ ጉንደት፣ ከዶጋሌ እስከ አምባላጌ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸዉ ነፃነት ሲሉ የተዋደቁባቸው  ታላላቅ ጀብዱዎችን የፈፀሙባቸው በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጎልተው የሚወጡ አውደ ውጊያዎች ናቸው፡፡

እ.ኤ.አ  ከህዳር 15 ቀን 1884 እስከ የካቲት 26፣1885 በጀርመን ዋና ከተማ በርሊን የአውሮፓ ሀያላን አፍሪካን በሰላማዊ መንገድ ለመቀራመት የሚገታን ማንም  የምድር ኃይል የለም ሲሉ የእብሪት ስምምነትን ተፈራረሙ፡፡ ይህ ከሆነ ከ12 ዓመታት በኋላ ግን ያልታሰበ እና ሊገምቱት እንኳን የማይችሉት የኢትዮጵያውያን ገድል በዓደዋ ላይ ተፈፀመ፡፡

የዓድዋ ድል የቀኝ አገዛዝ ማዕበልን የገታ፡ የቀኝ ገዢዎችን ቅስም የሰበረ፡ የጭቁን አፍሪካውያን እና የመላው ጥቁሮችን አንገት ቀና ያደረገ ድል ነው፡፡

ድሉ የኢጣሊያን ቅስም የሰበረውን ያህል፡ በእንግሊዝ ካምፕም ከባድ ሽብርን ነው የፈጠረው፡፡ የእንግሊዝ ስሌት ኢጣሊያ ኢትዮጲያን ተቆጣጥራ ፈረንሳይ ወደ ፈለገ አባይ የምታደርገውን መስፋፋት ታስቆምልኛለች የሚል እቅድ የነበራት ሲሆን ይህም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

ይህ የሰው ልጆች እኩልነት የተበሰረበት፡ የነፃነት ቀንዲል የሆነ ድል፡ እንደ ድሉ ግዝፈት ብዙ ያልተባለለት፡ በድሉ ላይ ታላቅ የዓለማች ጀብዱን የፈፀሙ ያልተዘመረላቸው ኢትዮጵያውያን ታሪክ   ተዳፍኖ ቆይቷል፡፡

የድሉ መግነጢሳዊ ሃይል ግን ሊደብቁትም ሆነ ሊያዳፍኑት የሚችሉት አልነበረም፤ ከዘመን ዘመን የሚፈካ አንፀባራቂ ገድል እንጂ፡፡

ስለ ዓደዋው ድል በቁጥር ብዙ ባይባሉም አንዳንድ የዓለማችን ታሪክ ፀሐፍት እና ሀያሲያን ክስተቱን በመዘገብ ለዓለም ማሕበረሰብ አስተዋውቀዋል፡፡

ከነዚህ መካክል አንዱ የታሪካ ምሁሩ ጆርጅ በርክለይ ሲሆን ፡The campaign of Adwa and The rise of Menelik በሚለው መፅሀፉ ስለ ዓድዋ ድል ፅፏል፡፡ ጆርጅ በርክለይ በአድዋ ጦርነት ትረካው ለጣሊያን ግልፅ ወገናዊነቱን ቢያሳይም የድሉን ግዝፈት ግን መካድ አልቻለም፡፡

ካለፈው የታሪክ ትንታኔ አኳያ የዓድዋ ጦርነት በአፍሪካ ምድር አዲስ ሃይል መነሳቱን ያሳያል የሚለው ጆርጅ በርክለይ፡ የዚች አህጉር ተወላጆች የማይናቅ ወታደራዊ ኃይል መሆን እንደሚችሉ ልናሰላስል ተገደናል ይላል፡፡እንዲያውም ነገሩ አስቂኝ ቢመስልም ይህ ሁኔታ ጭለማይቱ አህጉር አፍሪካ በላያዋ ላይ ስልጣኑን ባንሰራፋው አውሮፓ ላይ የምታደርገው አመፅ የመጀመሪያ ምዕራፍ ነው ይላል የታሪክ ፀሐፊው ጆርጅ በርክለይ ስለ ዓድዋው ድል ሲያትት፡፡

ሌላው በአደዋ ላይ የፃፉት ፤በዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ፀሐፊው ፕሮፌሰር ሬሞንድ ጆናስ ሲሆኑ፤ The Battle of Adwa African victory in the age of empire በሚለው መፀሐፋቸው ፤የአድዋ ድል ለኢጣሊያኖች መራራ ሽንፈት ነው ይላሉ፤የአውሮፓ ሃይል በጦር ሜዳ  በጥቁሮች ሲሸነፍ  አድዋ የመጀመሪያ መሆኑ ድሉን ለየት እንደሚያደርገው ሲገልፅ፤ አድዋ በዓለም ላይ አዲስ ፍሽን አዲስ ሴናሪዮ የፈጠረ ነው ይላሉ፡፡

ድሉ የአፍሪካ ጦር የአውሮፓ ሃይል መሸነፍ  ብቻ ሳይሆን ጥቁር ነጭን ያሸነፈበት ነው ሲሉ ይህም የአውሮፓውያን የበላይነት እና ገናናነት እያከተመ ለመምጣቱ ፍንጭ የሰጠ ነው ይላሉ፡፡

በኢጣሊያ ሀገር የሽንፈቱ ወሬ እንደተሰማ መቶ ሺህ የሚሆኑ ዜጎች ፊርማ በማሰባሰብ የጣሊያን ጦር ከአፍሪካ ሙለ ለሙሉ ለቆ እንዲወጣ ጠየቁ፡፡ የቀኝ ግዛት ፖሊሲ አቀንቃኙ ጠቅላይ ሚኒስትር ፍራንቺስኮ ክርሲፒ በፍጥነት ከስልጣናቸው እንዲወርዱ ተደረገ፡፡ ከጦርነቱ በፊት አጤ ምኒልክን በንብ ቀፎ ውስጥ አስሬ ሮም ድረስ አመጣለሁ ብሎ ፎክሮ የነበረው የኢጣሊያን ጦር መሪ ጀነራል ኦሬስቴ ባራቴዬሪ ለሽንፈቱ ዋንኛ ተጠያቂ በመሆን ፍርድ ቤት ቀረበ፡፡

እዉቁ የታሪክ ፀሐፊ እና ተመራማሪ ፕሮፈሰር ባህሩ ዘውዴ ”የዓድዋ ድል በታሪክ ያለው ስፍራ” ሲሉ በፃፉት ፅሁፍ፡ ዐደዋ ልዩ ትኩረት የተሰጠው ጥቁሮች በነጮች ላይ የተጎናፀፉት ዐቢይ ወታደራዊ ድል በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡ በዚህ ረገድ ከ10 ዓመት በኋላ የነጩን ዓለም እንደገና ለማናወጥ የበቃው ጃፓን በሩሲያ ላይ ያገኘችው ድል መቅደሙ ነበር ይላሉ፡፡የዓደዋው አብነት የነጭ የበላይነት አስከፊ የዘር መድልዎ ፖሊሲ በተንሰራፋባቸው አከባቢዎች የላቀ ነው ይላሉ፡፡ በእነዚህ ሀገሮች ለሚገኙ ጥቁሮች የዓድዋ ባለድል የሆነችው ኢትዮጵያ የነፃነት እና የክብር ፋና መሆኗን ይገልፃሉ፡፡ቀድሞውንም በመጽሀፍ ቅዱስ በስፋት የምትወሳው ኢትዮጵያ ”ኢትዮጵያኒዝም ” የተባለ ከነጮች ነፃ  የሆነ የጥቁሮች የኃይማኖት መነሳት መንስኤ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የዓድዋ ድል ስነ -ልቦና የአልገዛም ባይነት ፅናት እና ጥንካሬ  ከትውልድ  ወደ ትውለድ የሚጋባ ለአሁኗ ኢትዮጵያ በአንድነት ፀንቶ መቆም መሰረት ሲሆን ፤የአሁኑ ትውልድም በየዘመኑ የየእራሱ ዓደዋ ታሪክ ለመፃፍ ከለፉት አባቶቹ ወኔ እና ብርታትን ሰንቆ የኢትዮጵያን አንድነት እና ነፃነት ጠብቆ ከማቆየት በሻገር  የድህነት ቀንበር ለመስበር በየተሰማራበት መስክ ጠንክሮ ሊሰራ ይገባል፡፡