የሀረሪ ክልል ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለማድረግ ወስነ

የካቲት 12/ 2013 (ዋልታ) – የሀረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለማድረግ መወሰኑ ተገለጸ።

የክልሉ ካቢኔ ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርን ለመደገፍ የ12 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረግ በሚቻልበት ጉዳዮች ላይ መክሯል።

በዚህም መሰረት ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር 10 ሚሊዮን ብር የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ወስኗል።

በትግራይ ክልል ለሚገኙ የተጎዱ ዜጎች ደግሞ ከ2 ሚሊየን ብር በላይ የገንዘብ መጠን የሚገመት 70 ቦንዳ አልባሳት፣ 300 ኩንታል የምግብ ዱቄት እና የተለያዩ መጠን ያላቸው ሌሎች ለምግብ ፍጆታ የሚውሉ ድጋፍ እንዲደረግ ካቢኔው በሙሉ ድምፅ መወሰኑ ተገልጿል።

በተጨማሪም በትግራይ ክልል ያለውን የጤና አገልግሎት ለመደገፍ አንድ አምቡላንስ ተሽከርካሪ እና የጤና ባለሞያዎች ቡድንንን ወደ ስፍራው ለመላክ መወሰኑን የሃረሪ ክልል የመንግስት ጉዳዮች ኮሚኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል።

በሀረሪ ክልል ደረጃ የተዘጋጀውን ድጋፍ ወደ ስፍራው የሚያደርስ የልዑካን ቡድን በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ትግራይ ክልል እንደሚያቀናም ተገልጿል።
(ምንጭ፡- ኢዜአ)