የሀረሪ ክልል በሃይማኖትና ብሔር ሽፋን ግጭት ለመፍጠር በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ

ሚያዝያ 24/2014 (ዋልታ) በሀረሪ ክልል በሃይማኖትና በብሔር ሽፋን ሕዝቦችን መካከል ግጭት ለመፍጠር በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ የክልሉ መንግሥት አስታወቀ።
የሀረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በወቅታ ጉዳይ ላይ የአቋም መግለጫ አውጥቷል።
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።
በሐይማኖትና በብሄር ሽፋን ሕዝቦችን በማጋጨት አገር የማፍረስ ሴራ መቼም አይሳካም!
የሀገራችን ታሪካዊ የውጪ ጠላቶች ሀገር ለማፍረስ ከሚጠቀሙባቸው መንገዶች መካከል የሃይማኖት ፅንፈኝነትና አክራሪነትና በዋናነት ይጠቀሳሉ።
በሐይማኖትና በብሄር ሽፋን በሀረሪ ክልል ለዘመናት በሰላም፣ በፍቅር፣ በመቻቻልና በአብሮነት የኖረ እና እየኖረ የሚገኘውን ህዝብ በመከፋፈል ለማጋጨት እና ክልሉን የሁከትና የጦርነት ማዕከል ለማድረግ በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ ይወሰዳል።
በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ሃይማኖትንና ብሄርን ሽፋን በማድረግ እንዲሁም በሌሎች መንገዶች ሁከትና ብጥብጥን ለመፍጠር በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ የክልሉ መንግስት የጀመረውን ህግና ስርዓት የማስከበር ስራ እና የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ እንቅስቃሴ አጠናክሮ ይቀጥላል።
ይህንን ተግባር ለማፈፀምም የክልሉ መንግስት ሙሉ ቁርጠኝነትና ጠንካራ አቅም እንዳለው በዚህ አጋጣሚ መገንዘብ ያስፈልጋል።
በየደረጃው የሚገኙ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ታዋቂ ግለሰቦች የጥፋት ሀይሎችን ሴራ በማውገዝ የአካባቢያቸውን ሰላም እና ደህንነት ማስጠበቅ ይኖርባቸዋል።
ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ1443ኛው ኢድ አልፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ።
በድጋሚ ኢድ ሙባረክ!
የሀረሪ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት
ሚያዚያ 24/2014
ሐረር