ግንቦት 19/2013 (ዋልታ) – የሀገር በቀል እሴቶች ለዘላቂ ሰላም ግንባታ፣ አብሮነትና ብሔራዊ መግባባት ትልቅ ትርጉም አላቸው ሲሉ የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል ተናገሩ።
ከሁለት አመት በፊት በደረሰው የአውሮፕላን አደጋ ሰብአዊነት ያሳዩ ሰዎች “የሰውነት ተምሳሌቶች” ናቸው በሚል ተመስግነዋል።
የምስጋና ፕሮግራሙን ሰላም ሚኒስቴር፣ ዕርቀ ሰላም ኮሚሽንና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አደጋው ደርሶበት በነበረው ስፍራ በመገኘት አከናውነዋል።
የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል በስፍራው በመገኘት “የሰውነት ተምሳሌቶች” ለሆኑ ሁሉ ምስጋና አቅርበው፣ “የአካባቢው ነዋሪዎች የሰውነት መምህራን ናችሁ፤ የተጎጂ ቤተሰቦች መጽናኛ፣ ኢትዮጵያዊነትን በዓለም የሚያስተዋወቅ ዘመን ተሻጋሪ ተግባር ፈጽማችኋል” ብለዋል።
“ለዚህ ሰብዓዊ ተግባራችሁ እናመሰግናችኋለን፤ ምስጋናና ዕውቅና የመስጠት ስራውም የመስሪያ ቤቱ ብሔራዊ መግባባት መፍጠሪያ አንዱ አካል ነው” ብለዋል።
በንግግራቸው የሀገር በቀል እሴቶች ለዘላቂ ሰላም ግንባታ፣ አብሮነትና ብሔራዊ መግባባት ትልቅ ትርጉም ያላቸው መሆኑንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵየ ዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ሰብሳቢ ብፅዑ ካርዲናል አባ ብርሐነ ኢየሱስ ሱራፌል፣ አሁን አሁን በኢትዮጵያ ሰብዓዊነት እየተሸረሸረ መምጣቱን እየተመለከትን ነው ብለዋል።
ከሁለት አመት በፊት በደረሰው የአውሮፕላን አደጋ ሰብአዊነት ያሳዩት የቱሉ ፈራ ቀበሌና አካባቢው ነዋሪዎች ግን የሰብዓዊነት አይነተኛ ማሳያዎች ናቸው ብለዋል።
እንዲህ አይነት መልካም አሴቶችን ለመሸርሸር የሚሹ አካላት ቢያጋጥሙም በመልካም ምግባርና ስራቸው “የሰውነት ተምሳሌቶች” መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አቶ አላምረው ይርዳው በበኩላቸው፣ የግምቢቹ ወረዳ ቱሉ ፈራ ቀበሌ በሰብአዊነት ያሳዩት ተግባር ትልቅ ትምህርት ሰጥቶናል ብለዋል።
የተጎጂ ቤተሰብ ተወካዮችም 157 ተጎጂ ነፍሶችን በማክበርና በመዘከር ትልቅ ነገር ፈፅማችኋል፤ እናመሰግናለን ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ከጥዋቱ 2.00 መነሻውን ከአዲስ አበባ አድርጎ ወደ ናይሮቢ ሲበር የነበረ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ-8 አውሮፕላን በምስራቅ ሸዋ ዞን ግምቢቹ ወረዳ ቱሉ ፈራ ቀበሌ ተከስክሶ 157 የተለያዩ አገራት ዜጎች ሕይወት ማለፉ አይዘነጋም።