የህወሃት ቡድን በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ አዳዲስ ጥቃቶችን በመክፈቱ የስደተኞች ህይወት አደጋ ላይ መውደቁ ተገለጸ

ሐምሌ 07/2013 (ዋልታ) – አሸባሪው የህወሃት ቡድን በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ አዳዲስ ጥቃቶችን በመክፈቱ የስደተኞች ህይወት አደጋ ላይ መውደቁን የኢፌዴሪ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ችግሩን ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ከዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ የሚጠበቀውን ድጋፍ እንዳላገኘ ተገልጿል።

ኤጀንሲው ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በጥቃቱ ምክንያት በማይ-ዓይኒ እና በአዲ-ሐሩሽ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙት ኤርትራዊያን ስደተኞች ደህንነታቸው ላይ አደጋ ላይ ወድቋል።

ስደተኞቹ በዚህም የተነሳ ደህንነታቸው ሊጠበቅ ወደሚችልባቸው አካባቢዎች እንዲዛወሩ፣ በድጋፍ ላይ የተመሠረተ የከተማ ስደተኝነት እውቅና እንዲሰጣቸው እና ወደ ሶስተኛ ሀገር እንዲዛወሩ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጥያቄ እያቀረቡ እንደሆነ ኤጀንሲው ገልጿል።

ስደተኞችን ተቀብሎ በማስተናገድ ዘመን የተሻገረ ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ የስደተኞቹን ደህንነት ለመጠበቅ ጥረት እያደረገች እንደምትገኝም አመልክቷል።

“በቅርቡ ከሽሬ ለመውጣት ጥያቄ ያቀረቡ 79 ስደተኞች ወደ በራህሌ እንዲጓጓዙ ለተባበሩት መንግስታት (ተመድ) የስደተኞች ጉዳይ ኤጀንሲ (UNHCR) ጥያቄ ያቀረብንና ለዚህም በቅርበት እየሰራን ሲሆን ተጨማሪ ተመሳሳይ ፍላጎቶችን በተመለከተም አስፈላጊ ክትትሎችን በማድረግ ላይ እንገኛለን” ብሏል።

በተጨማሪም ሽመልባ እና ህፃፅን ለቀው ለወጡ ስደተኞች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ከተመድ የስደተኞች ጉዳይ ኤጀንሲ ጋር በመቀናጀት በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ ዓለም-ዋጭ ተብሎ በሚጠራ ቦታ አዲስ የመጠለያ ጣቢያ በማቋቋም ሂደት ላይ እንደሚገኝ ጠቁሟል።

ሆኖም ግን ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚጠበቀው ድጋፍ አለመገኘቱ ሂደቱ በተጠበቀው ደረጃ እንዳይሳለጥ አድርጎታል፡፡

በመንግሥት በኩል እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን እና ለውጦችን በመረዳት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ውጤታማ እና ተጨባጭ ድጋፎችን በማድረግ ስደተኞችን በአዲስ መጠለያ ጣቢያ የማስፈሩን ሂደት ለማፋጠን የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙ ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ መንግስት ለስደተኞች ደህንነት የሚያደርገውን ጥበቃ ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጦ፤ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተመዘገቡት የበቀል ጥቃቶች፣ አፈናዎች፣ እስሮች እና ሁከቶች ላይ የሚደረጉ ምርመራዎችን እንዲደግፍ ጥሪ አቅርቧል።

በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ የሚደርሰውን ስቃይ እና ግድያ በአንድነት እንዲያወግዝ ጥሪውን አስተላልፏል።

ከኤጀንሲው በኢትዮጵያ የኤርትራ ስደተኞችን ሁኔታ በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ስደተኞችን ተቀብለው በማስተናገድ እና ደህንነታቸውን በመጠበቅ የኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝብ ዘመናትን የተሻገረ ታሪክ ባለቤት ናቸው፡፡ ስደተኞቹ ወደ ትውልድ ቀያቸው ወደሚኖሩበት አካባቢ ሲመለሱ በተለይም ለአፍሪካ ቀንድም ሆነ ለቀሪው ዓለም ሰላምና ብልጽግና የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እንዲያደርጉ መንግሥት ጠንክሮ እየሠራ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በዋናነት ከጎረቤት ደቡብ ሱዳን ፣ ሶማሊያ ፣ ኤርትራ እና ሱዳን የመጡ ከዘጠኝ መቶ ሽህ በላይ ስደተኞች በማስተናገድ ላይ ትገኛለች፡፡

ከእነዚህን እውነታዎች በተቃረነ መልኩ በትግራይ ክልል ውስጥ በኤርትራ ስደተኞች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት የተመለከቱ ዘገባዎች ከተለያዩ አቅጣጫዎች እየወጡ ነው፡፡ ችግሩን ከመነሻው ለመመልከት ያስችል ዘንድ የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ ግንባር (ህወሃት) ኃይሎች በስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት ማድረስ የጀመሩት ከህዳር 2013 ዓ.ም. ጀምረው ሲሆን በተለይም በሁለት የኤርትራውያን የስደተኛ መጠለያዎች፣ ማለትም ሽመልባ እና ህፃፅ ላይ ያነጣጠረ እና የስደተኛ አገልግሎቱ ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጥ እና ስደተኞቹ ወደተለያዩ አካባቢዎች እንዲበተኑ እንዳደረገ ይታወቃል፡፡

የሕግ ማስከበር ሥራውን ተከትሎም ማይ-አይኒ እና አዲ-ሐሩሽ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ለሚገኙ ስደተኞች መደበኛ አገልግሎት መስጠትን ከመጀመር አንስቶ በትግራይ ክልል ተበታትነው የሚገኙ እና አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው አገሪቱ ወደሚገኙ ከተሞች የፈለሱ ስደተኞች ያሉባቸውን አካባቢዎች የመለየት ሥራ ተከናውኗል፡፡ ስደተኞችን ወደ ተረጋጋ ህይወት ለመመለስ መንግሥት ባደረገው ጥረት ወደ 9,000 የሚጠጉትን በማይ-ዓይኒ እና አዲ-ሀሩሽ በማስጠለል አስፈላጊውን የሰብአዊ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል፡፡ ስደተኞች የደህንነት ስሜት እንዲያዳብሩ ለማገዝ የስደተኞች ደህንነት ጥበቃ ጥረት አካል የሆነ የመጠለያ ጣቢያዎች ፀጥታ የማስፈን ሥራዎችም በተከታታይ እዲከናወኑ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ በተጨማሪም ከተጠቀሱት መጠለያ ጣቢያዎች የፈለሱ በአዲስ አበባ ብቻ ከ 5,200 በላይ ስደተኞች የተመዘገቡ ሲሆን አሁንም ምዝገባው እንደቀጠለ ይገኛል፡፡ ጥረቱን በማስፋትም በርካታ ስደተኞችን ወደ አፋር ክልል በራህሌ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ለማዘዋወር ተችሏል፡፡

በቅርቡ ከሽሬ ለመውጣት ጥያቄ ያቀረቡ 79 ስደተኞች ወደ በራህሌ እንዲጓጓዙ ለተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ኤጀንሲ (UNHCR) ጥያቄ ያቀረብንና ለዚህም በቅርበት እየሰራን ሲሆን ተጨማሪ ተመሳሳይ ፍላጎቶችን በተመለከተም አስፈላጊ ክትትሎችን በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡

በተጨማሪም ሽመልባ እና ህፃፅን ለቀው ለወጡ ስደተኞች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ከተ.መ.ድ የስደተኞች ጉዳይ ኤጀንሲ ጋር በመቀናጀት በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ ዓለም-ዋጭ ተብሎ በሚጠራ ቦታ አዲስ የመጠለያ ጣቢያ በማቋቋም ሂደት ላይ እንገኛለን፡፡ ሆኖም ግን ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚጠበቀው ድጋፍ አለመገኘቱ ሂደቱ በተጠበቀው ደረጃ እንዳይሳለጥ አድርጎታል፡፡

አሁን ህወሃት በመንግስት የተላለፈውን የተናጠል የሰብዓዊ የተኩስ አቁም ውሳኔ ውድቅ በማድረግ ስደተኞች በሰፈሩባቸው አካባቢዎች ሳይቀር አዳዲስ ጥቃቶችን መክፈቱ ግልፅ እየሆነ መጥቷል፡፡ በዚህ ምክንያት በማይ-ዓይኒ እና በአዲ-ሐሩሽ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙት ኤርትራዊያን ስደተኞች ደህንነታቸው ላይ አደጋ ላይ እንደወደቀ እንዲሰማቸው እና በዚህም የተነሳ ደህንነታቸው ሊጠበቅ ወደሚችልባቸው አካባቢዎች እንዲዛወሩ፣ በድጋፍ ላይ የተመሠረተ የከተማ ስደተኝነት እውቅና እንዲሰጣቸው እና ወደ ሶስተኛ ሀገር እንዲዛወሩ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጥያቄ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡

በዚሁ መሠረት ከስደተኞች ተወካዮች ጋር ተከታታይ ውይይቶችን ያካሄድን ሲሆን፣ በሐምሌ 06 ቀን 2013 ዓ.ም በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽነር የኢትዮጵያ ተወካይ በተገኙበት በመመስረት ላይ በሚገኘው የስደተኞች መጠለያ በሚገኝበት ዓለም-ዋጭ በመገኘት ከስደተኛ ተወካዮች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ መንግስት የስደተኞች ድምጽ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ይደመጣል በሚል ተስፋ በአዲሱ መጠለያ ጣቢያ ለማስፈር እና በድጋፍ ላይ የተመሠረተ የከተማ ስደተኝነት እውቅና ለመስጠት ጠንክሮ እየሠራ ይገኛል፡፡ በመንግሥት በኩል እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን እና ለውጦችን በመረዳት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ውጤታማ እና ተጨባጭ ድጋፎችን በማድረግ ስደተኞችን በአዲስ መጠለያ ጣቢያ የማስፈሩን ሂደት ለማፋጠን የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ለስደተኞች ደህንነት የሚያደርገውን ጥበቃ ለማስቀጠል ያለውን ቁርጠኝነት እያረጋገጠ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተዘገቡት የበቀል ጥቃቶች፣ አፈናዎች፣ እስሮች እና ሁከቶች ላይ የሚደረጉ ምርመራዎችን እንዲደግፍ ጥሪ በማቅረብ በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ የሚደርሰውን ስቃይ እና ግድያ በአንድነት እንዲያወግዝ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

ሐምሌ 07፣ 2013 ዓ.ም