የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድሩ የኢትዮጵያን ጥቅም አስጠብቆ እንዲጠናቀቅ እንሰራለን – አምባሳደሮች

የካቲት 18/2013 (ዋልታ) – የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር የኢትዮጵያን ጥቅም አስጠብቆ እንዲጠናቀቅ እንደሚሰሩ በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ እና በሴኔጋል የኢትዮጰያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደሮች ተናገሩ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት አምባሳደሮች የአፍሪካ ህብረትና ሌሎች ተቋማት ግድቡን በተመለከተ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ ንቁ ተሳታፊ እንደሚሆኑም አረጋግጠዋል።

በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ወይንሸት ታደለ ግድቡ የህልውና ጉዳይ እንደመሆኑ ”የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስጠበቅ በትጋት እሰራለሁ” ብለዋል።

በሴኔጋል የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መላኩ ለገሰ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከሴኔጋል ጋር ያላትን የረጅም ጊዜ ግንኙነት ወደተሻለ ትብብር ለመቀየር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

“የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላ አፍሪካ ትልቅ ኩራት በመሆኑ አገሮች ከፉክክር ይልቅ በትብብር መንፈስ ከሰሩ ከመልማት የሚያግዳቸው እንዳማይኖር አስረዳለሁ” ነው ያሉት።