መስከረም 20/2015 (ዋልታ) ዐቃቤ ሕግ የሐሰት ወሬን ነዝተዋል፣ በውጊያ ውስጥ የወገን ጦር አሰላለፍ እና ቦታን ለጠላት እና ለሕዝብ አሳውቀዋል በሚል እና በሌሎች ወንጀሎች የተጠረጠሩ ጎበዜ ሲሳይ፣ አሳየ ደርቤ እና መዓዛ መሐመድ የተባሉ ግለሰቦች ላይ በዛሬው ዕለት ክስ መመሥረቱን የፍትሕ ሚኒስቴር አስታወቀ።
1ኛ ተከሳሽ በሆነው ጎበዜ ሲሳይ፤ አሸባሪው (ህወሓት) ነሐሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም ለሦስተኛ ጊዜ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት መፈፀሙ በይፋ ተነግሮ የመከላከል እርምጃ እና ሕግ ማስከበር ዘመቻ ላይ የሕዝቡን ሞራል ዝቅ ለማድረግ በማሰብ በትዊተር ገጽ ላይ “Amhara Perspective” ተብሎ የተከፈተ የትዊተር አካውንት ላይ በቀን 26/12/2014 ቀርቦ ባደረገው ንግግር ጠቅላላ ሕዝቡ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን የማይደግፍ ይልቁንም ህወሓት ወደ አዲስ አበባ እንዲመጣ የሚፈልግ እና የሚደግፍ እና ወጣቱ ከመንግሥት ጎን መሰለፍ የማይፈልግ አድርጎ በማቅረብ ሠራዊቱ በአካባቢው ያለ ሕዝብ አይደግፈኝም ብሎ እንዲያስብ በማነሳሳት በሕዝብና እና በሠራዊት መካከል ያለውን መልካም ግንኙነት የሚጎዳ እሳቤ እንዲኖር የሠራ፣ የመንግሥት የመከላከል አቅም ላይ ሕዝቡ ያለውን አቋም የሚያፈርስ መረጃ ያስተላለፈ በመሆኑ የክስ ዝርዝር ቀርቦበታል።
በሌላ በኩል በራሱ ስም በከፈተው የፌስቡክ አካውንት በቀን 30/12/2014 ዓ.ም “አሁን በተከፈተው ጦርነት ውስጥም ህወሓትን ፊት ለፊት እየተዋጉ የሚገኙት የፋኖ መሪዎችን ምሬ ወዳጆን እና ደምሌ አራጋውን ለመግደል በተደጋጋሚ ከኋላ እየተተኮሰባቸው ህይዎታቸው ተርፏል።
በዚህ ሁኔታ እንዴት መንግሥትን ተማምኜ ጦርነት እገባለሁ የሚል ወጣትም አለ።” በማለት ትክክል አለመሆኑን እያወቀ የሐሰት ወሬ የነዛ በመሆኑ በተጨማሪም ነሐሴ 30/1014 ዓ.ም በፌስቡክ ገጹ በለጠፈው ጽሑፍ የሀገር መከላከያ ሠራዊቱ እና ጥምር ጦሩ የት አካባቢ እንዳለ እና የት አካባቢ ሳይዝ እንደቀረ በጽሑፉ በመግለጽ በውጊያ እንቅስቃሴ ውስጥ የወገን ጦር አሰላለፍ እና ቦታ ከፍተኛ ቁምነገር ሆኖ መያዝ የሚገባውን ለጠላት እና ለሕዝቡ በማጋራት ወንጀል አጠቃላይ 3 ተደራራቢ ክሶች ተመሥርተውበታል።
2ኛ ተከሳሽ አሳዬ ደርቤ እና 3ኛ ተከሳሽ መዓዛ መሐመድ ደግሞ በሮሃ ሚዲያ አማካኝነት ነሐሴ 19/2014 ዓ.ም ባደረጉት ቃለ ምልልስ “የነበረውን ጦርነት ማጠናቀቅ ይቻል ነበር። ችግሩ ምንድን ነው ለመሸነፍ ዝግጁ ያልሆነ ጠላት ስላጋጠመን ሳይሆን ፍላጎት የሌለው መንግሥት ስለነበረን ነው። ህወሓት ሲዳከም እፎይታ ጊዜ እየሰጠ ወደ ደቡብ ጎንደር ሲያመራ አፈግፍግ የሚል ትዕዛዝ እየሰጠ በሀብት የሚጠናከርበትን፣ የሕዝብ ሥነልቦና የሚንኮታኮትበትን መንገድ ሲጠርግ ነበር፣ ሕዝቡ ተጠናክሮ ከደቡብ ጎንደር ሲያወጣው ደግሞ በዛው ግለት ከማስቀጠል አንፃር የእፎይታ ጊዜ እየሰጠ እንደገና ወደ ወሎ የሚሄዱበትን መንገድ ሲያመቻች ነበር። እና የወንበር ስጋት ሲሆኑ ቀጥቅጦ ያባርራቸዋል፤ ከወንበሩ የሆነ ኪሎሜትር ርቀት ላይ ሲሆኑ ትቷቸው ይመጣል ማለት ነው” ብሎ በመናገር በወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አቅም እና ስልቶች ምክንያት የሚወሰኑ ውሳኔዎችን ፍፁም ሐሰት በሆነ መንገድ በመቀየር መንግሥት ሆነ ብሎ ህወሓት ሲዳከም ጥቃት የሚያቆም እና እንዲጠናከር ዕድል የሚሰጥ፣ ለማሸነፍ ፍፁም ፍላጎት የሌለው አድርጎ በማቅረብ የሐሰት ወሬዎችን በመንዛት 2ኛ ተከሳሽ የሐሰት ወሬዎችን 3ኛ ተከሳሽ በምታስተዳድረው ማኅበራዊ ሚዲያ ለማኅበረሰብ በማድረስ እና የሐሰት ወሬዎች እንዲሠራጩ በማድረግ ወንጀል መስከረም 20/2015 ዓ.ም በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ዐቃቤ ሕግ ክስ መሥርቶባቸዋል።
ይኸው የዐቃቤ ሕግ ክስ ፍርድ ቤት ደርሶ የመዝገብ ቁጥር የያዘ ሲሆን የፊታችን ሰኞ መስከረም 23 ቀን 2015 ዓ.ም ክሱ ለተከሳሽ እና የችሎት ታዳሚ ተነቦ ክርክሩ የሚቀጥል ይሆናል ሲል የፍትሕ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!