የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፈ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

ሐምሌ 12/2013 (ዋልታ) – የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፏል።

የምክር ቤቱ የደስታ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

“የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የታላቁ የሕዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር ውኃ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ በመጠናቀቁ የተሰማውን ልባዊ ደስታ ለመላው የሀገራችን ሕዝቦች ይገልጻል!

ምክር ቤቱ ደስታውን በተለያዩ ክፍለ-ዓለማት ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ለወዳጅ ሀገራት እና ግለሰቦች ሁሉ በታላቅ ኩራት እና ሀገራዊ ስሜት በድጋሚ ያበስራል!

ውድ የሀገራችን ሕዝቦች

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የአንድነታችን ማኅተም፣ የለውጥ ጉዟችን አውታር እንዲሁም የላባችን እና የጥረታችን ማሳያ እንደሆነ ከእኛ አልፎ መላው ዓለም ተረድቶታል፡፡

ይህም በቅርቡ በመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ባሰማነው የፍትሐዊነት ሐሳብ፤ ዓላማችን በጋራ ሀብት የዕኩል ተጠቃሚነት መርህ መከተል መሆኑን በማያወላዳ አኳኋን ለሚመለከታቸው ሁሉ አስገንዝበናል፡፡

እናም ይህ የጀመርነው የልማት ጉዞ በሁሉም ዘርፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ምክር ቤቱ በአክብሮት ያሳስባል፡፡

በተለይም በአሁኑ ወቅት የውስጥ እና የውጭ ጠላቶቻችን ባለ በሌለ ዓቅማቸው ሀገራችንን ለማፈራረስ እየሠሩ ባሉበት ሁኔታ፤ የእኛ አንድ ሆኖ መቆም ምርጫ የሌለው አማራጭ መሆኑን መረዳት ይኖርብናል፡፡

ይህንንም በጽኑ ዕምነት አጠናክረን የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን በማድረግ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ይጠበቅብናል፡፡

በሌላ በኩል፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መላውን የሀገራችንን የእስልምና ሐይማኖት ተከታዮች እንኳን ለ1442ኛው ዓመተ-ሒጅራ የዒድ አል-አድሐ ዐረፋ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ይላል፡፡ እንኳን ለዐረፋ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!

በዓሉ በሚገርም ታሪካዊ ግጥምጥሞሽ ከ2ኛው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ውኃ ሙሌት ጋር መጣጣሙ ደግሞ፤ በዓሉን ልዩ አድርጎታል፡፡

ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ ያበረከተውን ወደር-የለሽ አስተዋጽዖ፤ ታሪክ መቼም አይረሳውም!

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት፤ ታፍራ እና ተከብራ ለዘለዓለም ትኖራለች!