የመስቀል በዓል ከደመራ ሥነ-ሥርዓት ጋር በጎንደር፣ በገንዳ ውሃና በሰቆጣ ዛሬ እየተከበረ ይገኛል

መስከረም 17/2016 (አዲስ ዋልታ) የመስቀል በዓል ከደመራ ሥነ-ሥርዓት ጋር በጎንደር፣ በገንዳ ውሃና በሰቆጣ ከተሞች ሃይማኖታዊ ስርዓቱንና ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መንገድ ዛሬ እየተከበረ ይገኛል፡፡

በጎንደር ከተማ እየተከበረ ባለው በዓል ላይ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ ዮሃንስ በዓሉን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ እግዚአብሄር የሰጠንን ዓመቱንና በዓላትን ለሰላምና ለአንድነት መጎልበት ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል፡፡

መስቀል የሰላም የአንድነትና የፍቅር ልዩ ምልክት በመሆኑ ሃይማኖታዊ እሴቱ ተጠብቆ ከትውልድ ትውልድ እንዲሻገር ህዝበ ክርስቲያኑ በአብሮነት መስራቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የጎንደር ከተማ ከንቲባ ተወካይ ግርማይ ልጃለም በበኩላቸው የመስቀል ደመራ በአል በሰላምና በደመቀ መልኩ መከበሩ የህዝቡን ሰላም ፈላጊነትና ጨዋነት አጉልቶ ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የመስቀል በዓል ስናከብር ጥላቻን በማስወገድ ፍቅርና አንድነትን በሚያፀና መልኩ መሆን እንዳለበት የገለፁት ደግሞ የምዕራብ ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶሱ አባል ብጹዕ አቡነ ሰላማ ናቸው።

በዓሉን ስናከብርም ያለው ለሌለው በማካፈልና ለወንድሙ ፍቅርን በመግለፅ መሆን እንዳለበት ጠቅሰው፤ ይህ በጎ ተግባር በዚህ ቀን ተወስኖ መቅረት እንደሌለበትም አሳስበዋል።

የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ አባተ ነጋ በበኩላቸው፤ የበዓሉ መገለጫ አንድነት፣ ፍቅርና ሰላም ነው ብለዋል።

ምዕመኑ በአደባባይ ወጥቶ በዓሉን እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ያሳለፈው ሰላም በመኖሩ ነውና ቀጣይም ሰላሙን ማስጠበቅ እንዳለበት ጠቁመዋል።

“በዓሉ ድምቀቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር በማድረግ የሌሎች እምነት ተከታዮችም ድርሻ የጎላ ነው” ያሉት ደግሞ የገንዳ ውሃ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አብዱልከሪም ሙሃመድ ናቸው።

በዓሉ በሰላምና በድምቀት እንዲከበር የከተማዋ ወጣት ላበረከቱት አስተዋፅኦ አመስግነው፤ በቀጣይም ይህን ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

በሌላ በኩል የመስቀል በዓል በዋግ ኽምራ ዞንና በሰቆጣ ከተማም በልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች እየተከበረ ነው።

የዋግ ኽምረ ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ በርናባስ እንዳሉት መስቀል የምህረት የፍቅር ተምሳሌት በመሆኑ ምእመኑ ለሰላም ዘብ መቆም አለበት።

 

የሰቆጣ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ መላሽ ወርቃለማው በበኩላቸው፤ በመስቀል በዓል የታየው አንድነትና መተባበር ተጠናክሮ በልማቱና በሌሎች ተግባራትም ሊቀጥል ይገባል ማታውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የመስቀል በአል በጎንደር፣ ገንዳ ውሃና ሰቆጣ ከተሞች የእምነቱ አባቶች፤ የየከተሞቹ አመራሮችና ምዕምናኑ በተገኙበት በድምቀት እየተከበረ ነው።