የመስቃን ወረዳ ለመከላከያ ሰራዊት ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተለያዩ ድጋፎች አደረገ

ጳጉሜ 2/2014 (ዋልታ) በጉራጌ ዞን የምስራቅ መስቃን ወረዳ ለአገር መከላከያ ሰራዊት ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ 15 ሰንጋዎችን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎች አደረገ።

የወረዳው ማኅበረሰብ አሸባሪው ህወሃት ለ3ኛው ጊዜ በኢትዮጵያ ላይ የከፈተውን ጦርነት ለመቀልበስ የድርሻውን ለመወጣት ያለውን ዝግጁነትም ማረጋገጡ ተገልጿል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ለመደገፍ የተቋቋመው ሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ እየተደረጉ ያሉ ድጋፎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቋል።

አሸባሪው ቡድን ሀገርን ለማፍረስ የከፈተውን ጦርነት ለመመከት እና የአገርን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ እየተዋደቀ ለሚገኘው ሰራዊት ኅብረተሰቡ አጋርነቱን በንቃት ማሳየቱ ተገልጿል።

በወረዳው በሁለት ቀናቶች ብቻ 15 ሰንጋዎች መዘጋጀታቸውንና እንዲሁም የወረዳው አመራሮችና የመንግስት ሰራተኞች ለሰራዊቱ ከደመወዛቸው ድጋፍ ማድረጋቸውን ኮሚቴው አመልክቷል።

የወረዳው ማህበረሰብ ከዚህ ቀደምም ለመከላከያ ሰራዊቱ ያለውን ድጋፍ በተግባር ማሳየቱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡