የመንግስት ተቋማት የንብረት ምዝገባ ሊካሄድ ነው

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ሃጂ ኢብሳ

ሚያዚያ 1 /2013 (ዋልታ) የ190 የፌዴራል የመንግስት ተቋማት የንብረት ምዝገባ ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ ሊካሄድ መሆኑን የመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ።

በተለያዩ ተቋማት ተከማችተው የሚገኙ ኬሚካሎችን ማስወገድ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ጥናት እየተካሄደ መሆኑም ተገልጿል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ሃጂ ኢብሳ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በሀገሪቷ 190 ፌዴራል የመንግስት ተቋማት የንብረት ምዝገባ ከሚያዝያ 4 እስከ 8 ቀን 2013 ዓ.ም ባሉት አምስት ቀናት ይከናወናል ብለዋል።
በተቋማቱ ምዝገባው ከተከናወነ በኋላ የሚወገዱት እንዳለ ሆኖ የሚያገለግሉት ያለስራ ተቀምጠው ከሆነ ለሌሎች ተቋማት ይተላለፋሉ ብለዋል።
ምዝገባውን ለማካሄድ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና ከኤጀንሲው የተውጣጣ አብይ ኮሚቴ መቋቋሙንም አቶ ሃጂ ገልፀዋል።
በምዝገባ ሂደቱ የሱፐርቪዥን ቡድን መቋቋሙን ጠቅሰው ምዝገባውን ቀደም በለው የጀመሩ ተቋማት እንዳሉም አመላክተዋል።
ምዝገባውን በተመለከተ ለሁሉም ተቋማት በደብዳቤ ከማሳወቅ በተጨማሪ ከግማሽ በላይ ለሆኑት ተቋማት በአካል በመገኘት የማሳወቅ ስራ ተሰርቷልም ብለዋል።
በቀጣይ ሳምንት አርብ የምዝገባውን ሂደትና ውጤታማነት ለህዝብ እናሳውቃለን ያሉት አቶ ሃጂ ከሚያዝያ 11 እስከ15 ቀን 2013 ዓ.ም በተቋማት ኅላፊዎች ተፈርመው የተመዘገቡት ሀብትና ንብረቶች ወደ ኤጀንሲው ይመጣሉ ብለዋል።