የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 94ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 94ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ምክር ቤቱ  የውጭ አገር ስራ ስምሪት ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ መክሮ ግብአቶች በማከል ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡

ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የኢትዮጵያ የውጭ ሀገር ስራ ስምሪት ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ሲሆን የኢትዮጵያ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት አዋጅ ቁጥር 923/2008 ተግባራዊ በሚደረግበት ጊዜ በአፈጻጸም ያጋጠሙ ስህተቶችን ማረም ተገቢ በመሆኑ፣ እንዲሁም አሁን ዘርፉ ከደረሰበት ነባራዊ ሁኔታ አኳያ አዋጁን ማሻሻል አስፈላጊነቱ ስለታመነበት የህጉን ክፍተቶች በጥናት በመለየትና የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ በመፈተሽ የማሻሻያ ረቂቅ ተዘጋጅቶ ቀርቧል ተብሏል፡፡
ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ መክሮ ግብአቶችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በኢትዮጵያና በኡጋንዳ መካከል የተደረጉ በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ የመስጠትና በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የፍትሕ  ትብብር ስምምነቶች ረቂቅ አዋጆች ላይ ውይይት ካደረገ በኋላ እንዲጸድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቷል፡፡

ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ በደቡብ አፍሪካ መካከል የተፈረመው የዲፕሎማቲክና ሰርቪስ ፓስፖርት  ለያዙ ሰዎች ቪዛን የማስቀረት ስምምነት ረቂቅ አዋጅ ላይም ውይይት ካደረገ በኋላ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስተላልፏል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ የሚሰጡ አገልግሎቶች የሚከፈል  የአገልግሎት ክፍያን ለመወሰን የወጣ ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቷል፡፡ ምክር ቤቱ በረቂት ደንቡ ላይ ከተወያያ በኋላ ደንቡ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡

ምክር ቤቱ የኢትዮ ቴሌኮም ማቋቋሚያ ደንብን ለማሻሻል የተዘጋጀ ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት አድርጎ ደንቡ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ስራ ላይ እንዲውል ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

በተጨማሪም ምክር ቤቱ ከዓለም አቀፍ የልማት ማህበር ጋር ለ5ኛው ምዕራፍ ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ማስፈጸሚያ እንዲውል የተፈረመውን የብድር ስምምነት ለማጽደቅ በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ እንዲጸድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቷል፡፡