የማዕድን ሃብትን በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ ለማዋል ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ

የካቲት 24/2015 (ዋልታ) የማዕድን ሃብትን በተገቢው መንገድ ለህዝብና ለሀገር ጥቅም ለማዋል ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን የማዕድን ሚኒስትር ሃብታሙ ተገኝ ገለጹ፡፡

የማዕድን ሚኒስትሩ ከሚኒስትር ዴኤታ ሚሊዮን ማቴዎስ እና የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ በዲማ ወረዳ ተገኝተው የኢትኖ ማይኒንግ ኩባንያን የሥራ እንቅስቃሴ የጎበኙ ሲሆን ስለ ባንያው አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ የኩባንያው ስራ አስኪያጅ አብራርተውላቸዋል፡፡

ኩባንያው ከ10 ዓመት በላይ በጋምቤላ ክልል ዲማ ወረዳ የወርቅ ፍለጋ በማካሄድ በአሁኑ ሰዓት 132 ጉድጓዶችን በመቆፈር ጥናት አድርጎ የልየታ ሥራና የተለያዩ የግንባታ ስራ መሥራቱን አስታውቀዋል፡፡

ኩባንያው በያዘው የጊዜ ገደብ ወደ ስራ እንዳይገባ የሲሚንቶ እጥረት እና ተያያዥ ጉዳዮች እንደገጠሙት የገለጹት ስራ አስኪያጁ በቀጣይ ችግሮቹን በመፍታት በ2 ወር ውስጥ የወርቅ ፋብሪካውን በመትከል ወርቅ ማምረት እንደሚጀምር መናገራቸውን የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡

የማዕድን ሚኒስትሩ ሃብታሙ ተገኝ በበኩላቸው የማዕድን ሃብቱን በተገቢው መንገድ ለህዝብና ለሀገር ጥቅም ለማዋል እንደሀገር ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸው የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት እና ማህበረሰቡ የማዕድን ሃብቱ ለሀገር ልማት እንዲውል የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጠይቀዋል።