ግንቦት 23/2013 (ዋልታ) – በአንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ወጪ በገላን ከተማ በሜልባ ፕሪንቲንግ ፐብሊሺንግና ፓኬጂንግ አክሲዮን ማህበር የተቋቋመው ዘመናዊ ማተሚያ ድርጅት ዛሬ በኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በይፋ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡
እንደ ኢፕድ ዘገባ በዘመናዊነቱ ከምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያ ነው የተባለው ማተሚያ ቤቱ በቀን 138 ሺህ መጻህፍት እንዲሁም በሰዓት ባለ 32 ገጽ የሆኑ 65 ሺህ መጽሄቶችን የማተም አቅም እንዳለው ተገልጿል።
ከገላን ከተማ አስተዳደር በተገኘ 23 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ መገንባቱን የማህበሩ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ዳባ ደበሌ አስታውቀዋል፡፡
ተቋሙ ለ900 ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠሩ የተገለጸ ሲሆን፤ በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።