የምርጫ ቦርድ ውጤት ማሳወቅ እና ማረጋገጫ መስጠት መጀመሩን አስታወቀ

መስከረም 25/2014 (ዋልታ) ምርጫ ቦርድ መስከረም 20 2014 ያካሄደውን ምርጫና ህዝበ ውሳኔ ውጤት ማዳመር እና ማረጋገጫ መስጠት መጀመሩን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሐረሪ፣ በሶማሌ እና በደ/ብ/ብ/ሕ ክልል ባካሄደው ምርጫና ሕዝበ ውሳኔ በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።

ቦርዱ በመግለጫው በምርጫ ሂደት የነበረውን አጠቃላይ ሁነቶችና ግኝቶች፤ የድምፅ አቆጣጠር እና ቀጣይ የውጤት ማሳወቂያ ሂደትን እያከናወነ መሆኑን ተናግሯል።

የቦርዱ የኮሚኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በሐረሪ፣ በሶማሌ እና በደቡብ ክልል እና ድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ያካሄደው ምርጫና ህዝበ ውሳኔ ድምፅ ውጤት በምርጫ ክልሎች በማዳመር ውጤቱ ወደ ማዕከል ተልኮ እና ማረጋገጫ የመስጠት ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም እስካሁንም ለሁለት የምርጫ ክልል ውጤቶች ቦርዱ ማረጋገጫ መስጠቱን የገለፁ ሲሆን ምርጫ ክልሎቹም በድሬደዋ እና በደቡብ ክልል የሚገኙ ናቸው ብለዋል።

በድሬደዋ ከተማ ምርጫ ክልል 1 ስር ያሉ ሁለት ምርጫ ጣቢያዎች ውጤት መሰረት ሶስት የብልፅግና እጩዎች ለክልል ም/ቤት አሸንፈዋል ነው ያሉት፡፡

እንዲሁም በደቡብ ክልል ባስኬቶ እና ጉመር ምርጫ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ማሸነፉንም ገልፀዋል።

የተቀሩ ምርጫ የተካሄደባቸው ምርጫ ክልል ውጤቶች በማዳመር ወደ ማዕከል እየተላኩ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን በአንዳንድ የመሰረተ ልማት ችግር ተጠናቀው ወደ ማዕከል ያልደረሱ ውጤቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።

በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤቶች ሙሉ በሙሉ ወደ ማዕከል እንደሚደርሱም ተገልጿል፡፡

(በደረሰ አማረ)