የካቲት 05/2013 (ዋልታ) የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሐረሪ ክልልና ድሬዳዋ አስተዳደር ለተውጣጡ የምርጫ አስፈጻሚዎች ያዘጋጀው ሥልጠና በድሬዳዋ ከተማ እየሰጠ ነው፡፡
በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ ዚያድ ያሲን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ መጪው ምርጫ ተአማኒና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የቅድመ ምርጫ ሂደቱ በግልጽነትና ተጠያቂነት እየተከናወነ ይገኛል፡፡
የቅድመ ምርጫ ሂደቱን አስመልክተው የትኛውም ፓርቲ የምርጫ ቦርድን ህግና ደንብ ተከትሎ ለሚያቀርበው ጥያቄ ቦርዱ በአግባቡ ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ምርጫ አስፈጻሚዎቹ በሚመለከታቸው አካላት ገለልተኛ መሆናቸው ይሁንታን ያገኙና ከተለያዩ ተቋማት የተመለመሉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ገለልተኛ መሆናቸው ተረጋግጦ ለተመለመሉ የድሬዳዋ አስተዳደርና ሐረሪ ክልል የምርጫ አስፈጻሚዎች ትላንት የተጀመረው ስልጠና ለተከታታይ ሶስት ቀናት እንደሚሰጥ አቶ ዚያድ ገልጸዋል፡፡
ሥልጠናው የዘንድሮ ምርጫ በቴክኖሎጂ ተደግፎ የሚካሄድ በመሆኑ በሥራ ላይ ችግር እንዳያጋጥማቸው ያግዛል ብለዋል፡፡
ከሥልጠናው በኋላም ሠልጣኞቹ ሥራ እንደሚጀምሩም ተናግረዋል፡፡
በተለዩ የምርጫ ክላስተሮች ለምዝገባ የሚሆኑ ቢሮዎች መዘጋጀታቸውንና አስፈላጊ ቁሶቁችም እየተሟሉ እንደሚገኙም አስታውቀዋል፡፡
የዕጩዎች ምዝገባ ከየካቲት 8 እስከ የካቲተ 21 ይካሄዳል።
እንደ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ መረጃ የዘንድሮ ምርጫ ፍፁም ሠላማዊ ፣ዲሞክራሲያዊ ፣ ህጉን ተከትሎ ተአማኒ ሆኖ ት እንዲጠናቀቅ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ፣ የህግና የፀጥታ አካላት፣ የሲቪክ ማዕከላት ያሉበት የጋራ ፎርም ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ ይገኛል፡፡
ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በምርጫው በመሳተፍ ሀገርን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማሻገር የዜግነት ኃላፊነቱን እንዲወጣ አቶ ዚያድ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
(ምንጭ ፡-ኢዜአ)