የምስራቅ አፍሪካ እና የአፍሪካ ቀንድ አገራት የፍልሰተኞች ጉዳይ የዳሰሳ ጥናት ሪፖርት ይፋ ሆነ

ሚያዝያ 25/2015 (ዋልታ) የምስራቅ አፍሪካ እና የአፍሪካ ቀንድ አገራት የፍልሰተኞች ጉዳይ የዳሰሳ ጥናት ሪፖርት በኬንያ ናይሮቢ ይፋ መደረጉን የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ።

የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በተገኙበት ይፋ የሆነው ሪፖርቱ የቀጣናው አገራት በጋራና በተናጠል የፍልሰተኞችን ሁኔታ ህጋዊ መስመር ለማስያዝ የሚያደርጉትን ጥረት ወደ አንድ ለማምጣት ፍኖተ ካርታ ሆኖ የሚያገለግል እንደሚሆን ተጠቁሟል።

የጥናቱ ሪፖርት በዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ጉዳይ ድርጅት (IOM)፣ በኢጋድ (IGAD) እና የምስራቅ አፍሪካ ኮሙዩኒቲ (EAC) በትብብር የተዘጋጀ መሆኑን ሚኒስትሯ አመልክተዋል።

ሚኒስትሯ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት በምስራቅ አፍሪካና ቀንድ አገራት የፍልሰተኞችን ሁኔታ በቅርበት በመከታተል፣ በማስተባበር እና በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ፍልሰትን በመደገፍ ለሚያደርጉት ድጋፍ የዓለም አቀፉን የፍልሰተኞች ጉዳይ ድርጅት (IOM)፣ ኢጋድ (IGAD) እንዲሁም የምስራቅ አፍሪካ ኮሙዩኒቲ (ECA) ላመሰግን እወዳለሁ ብለዋል።

የምስራቅ አፍሪካ እና ቀንድ አገራትን የትብብር ማዕቀፍ በፍልሰተኞች አስተዳደርም ሆነ በሌሎች ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮች መጠናከር ለመላው አፍሪካ በአንድ የመቆም ምሰሶ መሆኑም በሪፖርቱ ተመላክቷል።