የምክር ቤቱ አባላት ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ የላቀ ሚና ላበረከቱ ምስጋና አቀረቡ

ሰኔ 28/2013 (ዋልታ) – የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የላቀ ሚና ለተጫወቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት ጠላቶች ከውስጥና ከውጭ የኢትዮጵያን የለውጥ ጉዞ ለማደናቀፍ እየሰሩ ባለበት በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሃዊ የሆነ ምርጫ እንድታካሂድ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ፣ ኢትዮጵያ እንታሸንፍ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የፀጥታ አካላት እና የሚዲያ ተቋማት የነበራቸውን ገንቢ ሚና አድንቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሀገራዊ ምርጫው በተሳካ ሁኔታ እንዲናቀቅ ለሰጡት በሳል አመራርም የምክር ቤቱ አባላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ ልዩ ስብሰባው ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም የተካሄደው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ከዚህ በፊት የነበሩ ችግሮች የታረሙበት እና ህዝብ ብርድና ዝናብ ሳይበግረው በነቂስ ወጥቶ የተሳተፈበት መሆኑን በማንሳት የእንኳን ደስ አለን መልእክት አስተላለፈዋል፡፡

ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ ከመጠናቀቁም በላይ መራጮች በየምርጫ ክልላቸው ችግኞችን በመትከል አረጓጓዴ ዐሻራቸውን ያሳረፉበት መሆኑንም የምክር ቤቱ አባላት በአዎንታዊነት አንስተዋል፡፡

“ኢትዮጵያውያን በህዝቦች ተሳትፎ የተሳካ ሰላማዊ ምርጫ በማሄዳችን አንኳ ደስ አለን” ያሉት የምክር ቤቱ አባላት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሀገሪቱን ብልፅግና ለማረጋጥ የያዟቸው ውጥኖች እንዲሳኩ ፈጣሪ እንዲረዳቸው መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡