ጥር 24/2014 (ዋልታ) የምዕራብ ዕዝ የሽብር ቡድኑን መዋቅር በማፈራረስና የህግ ማስከበር ዘመቻው በአጭር ጊዜ እንዲቋጭ በማድረግ ረገድ የአንበሳውን ድርሻ መወጣቱን ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለፁ።
እዙ በ3 ደረጃዎች የሜዳልያ ሽልማት የሰጠ ሲሆን፤ በእውቅናው አመራርሮች፣ አባላትና ክፍሎች ተሸላሚ ሆነዋል።
በስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ለጀግኖች ሜዳልያ ከሸለሙ በኋላ ባደረጉት ንግግር፣ የምዕራብ ዕዝ በሰራዊታችን ላይ የክህደት ተግባር የፈፀመውን የአሸባሪውን ቡድን ቁንጮ ፖለቲካዊና ወታደራዊ አመራሮች በመደምሰስና በቁጥጥር ስር በማዋል የህግ ማስከበር ዘመቻው በአጭር ግዜ እንዲቋጭ የአንበሳውን ድርሻ የተወጣ እዝ ነው ብለዋል።
ተሸላሚዎቹ አገርን ከመፍረስ ለማዳን ባደረጉት ተጋድሎ ሽልማቱ እንደተሰጣቸው የገለፁት ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ፣ ሽልማቱ ለተመረጡ አባላት ቢሰጥም ስራው ግን የሁሉም አመራርና አባላት የጋራ ውጤት እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል ብለዋል። ለቀጣይ ግዳጅ ራስን ማዘጋጀት እንደሚጠበቅባቸውም በማስታወስ።
የምዕራብ ዕዝ አዛዥ ሌ/ጄ መሰለ መሰረት በበኩላቸው፣ የምዕራብ ዕዝ ላለፉት 15 ወራት የአሸባሪውን ቡድን አከርካሪ ለመስበር በሰው ሃይል፣ በቁሳቁስና በሞራል ደረጃ እንዲዳከም ያደረገና የሽብር ቡድኑ ሰሜን እዝ ላይ ያደረገውን አፈና የቀለበሰ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም በእግር ረጅም ርቀት በመጓዝ የተቋሙን ፍላጎት ያሳካ ዕዝ መሆኑን እና በዚህ ጦርነት በርካታ ጀግኖችን ማፍራት መቻሉን እና ለቀጣይ ግዳጅም በቂ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።
ከተሸላሚዎቹ መካከል አንዳንዶቹ፣ ሽልማቱ ለቀጣይ ግዳጅ ተጨማሪ ሃላፊነትን የሚያጎናፅፍ በመሆኑ ለሃገር ሉዓላዊነት መከበር አስፈላጊውን ሁሉ መስዋዕትነት እንደሚከፍሉ መናገራቸውን የመከላከያ ሰራዊቱ መረጃ አመልክቷል።