የም/ጠ/ሚ ደመቀ ሰብዓዊ ጉዳዮች ያተኮረ ውይይት

ም/ጠ/ሚ ደመቀ

መስከረም 12/2014 (ዋልታ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ዋና አስተባባሪ ማርቲን ግሪፍትስ ጋር በሰብዓዊ ድጋፍ ዙሪያ በኒውዮርክ ተገናኝተው ተወያዩ፡፡

በምክክሩም በሁሉም አካባቢዎች የሰብዓዊ አገልግሎት ለሚሹ ወገኖች ተደራሽ ለማድረግ በእርዳታ አሰጣጥ ሂደቱ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በፍጥነት መፍታት እንደሚገባ አቶ ደመቀ መኮንን አመልክተዋል።

በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ችግር ተከትሎ በአጎራባች አካባቢ የሚኖሩ ወገኖች ለችግር ተጋላጭነታቸው እየጨመረ በመምጣቱ ሁሉአቀፍ የሰብዓዊ አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ እንደሚጠይቅም ጠቁመዋል።

በሁሉም አካባቢዎች የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች በተሟላ አግባብ ተደራሽ ለማድረግ በእርዳታ አሰጣጥ ሂደቱ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በፍጥነት መፍታት እንደሚገባም ገልጸዋል።

የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎት እና አቅርቦት ባለው መስተጋብር የሚገጥሙ ክፍተቶችን ለመድፈን ቅንጅታዊ አሠራርን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጠይቅ አመላክተዋል።

ሁሉአቀፍ የሰብዓዊ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ መንግሥት የሚያደርገውን ርብርብ የዓለምአቀፉን ማኅበረሰብ ሚዛናዊ ግንዛቤ በማስጨበጥ ረገድ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

ጽሕፈት ቤቱም  በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት ከመንግሥት ጎን በመቆም ለሚያደርገው ድጋፍም አቶ ደመቀ አመስግነዋል።

በውይይቱ መንግሥት ለሰብዓዊ አገልግሎት አሰጣጥ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ረገድ ባደረገው ርብርብ ከጊዜ ወደ ጊዜ በርካታ ጉዳዮች እንደተሻሻሉ የጋራ ግንዛቤ መያዙን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።