የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪሃትና የእንግሊዝ መንግስት ልዩ መልእክተኛ ውይይት

መስከረም 15/2013 (ዋልታ) – የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል የእንግሊዝ መንግስት ልዩ መልእክተኛ ኒክ ዳየር የሚመራ የልዑካን ቡድን ጋር በወቅታዊ ሁኔታዎች ዙሪያ ተወያዩ፡፡
የፌደራል መንግስት ሀገራዊ ግዴታዎች በሚጥሉበት ህግጋትና የአለም አቀፍ መስፈርት በሚያስቀምጠው መሰረት ምግብ፣ መድሃኒትና ሌሎች ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁስን ለተጎዱ የትግራይ ክልል ዜጎች እንዲደርሳቸው በሚደረገው ጥረት ዙርያ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እየተወጣ እንደሆነና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም ጋር አቅርቦቱ የሚጠናከርበት መንገድ ላይ ውይይት መደረጉን ሚኒስትሯ አንስተዋል።
የአለም አቀፉ ማህበረሰብ እያበረከተ ያለው እርዳታ ውስንነትና ሰብአዊ ቀውስ ለደረሰባቸው የአፋርና አማራ ክልሎች በቂ ትኩረት መሰጠት እንዳለበትም ሚኒስትሯ ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ግጭቱን ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በማስፋፋትና ለእርዳታ አቅርቦት የተሰማሩ መኪኖችን ለጦርነት በማዋል እንቅፋት በመፍጠር፣ በዜጎች ረሀብና እንግልት የፖለቲካ ትርፍ ለማትረፈ የሚጥረውን ቡድን በአግባቡ መተቸት ለአለም አቀፉ ህብረተሰብ እንቆረቆራለን ለሚሉ አካላት የሞራል ግዴታ እንደሆነ አስረግጠው መግለጻቸውን ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።