የሰላም ዘርፍ የጋራ ምክክር መድረክ በጅግጅጋ ተካሄደ

የፌደራል፣ ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የሰላም ዘርፍ የጋራ ምክክር መድረክ  በጅግጅጋ ከተማ መካሄድ ጀመረ።

“የሰላም ቤተሰብ እርስዎ ኖት” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ በሚገኘው የውይይት መድረክ ላይ የሠላም ሚንስትር ሙፈሪያት ካሚል፣

የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሞሀመድ፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ  ኮሚቴ ሰብሳቢዎች፣ የፌደራል የክልልና የከተማ አስተዳደር የሰላም እና ፀጥታ አካላት አመራሮችና ባለድርሻዎች ታሳታፊ ናቸው።

የሰላም ሚንስትሯ  ሙፈሪያት ካሚል፣ በሶማሌ ክልል ባለፉት ሁለት አመት ተኩል የነበረውን አሰራር በመቀየር እና ሰላም በማስፈን የለውጡ አካል የሰራው ስራ ፍላጎትና ጥረት ካለ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ማሳያ ነው ብለዋል።

የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፌ ሞሀመድ፣ እውነተኛ ሰላምን በጦርና በጠ መንጃ ማስፈን እንደማይቻል ያለፈው ስርዓት ማሳያ ነው ብለዋል፤ የቀደመው ስርዓት የቀበረው የክፋት ፈንጂ በየጊዜው እየፈነዳ ሰላም እንዳያሳጣን ተግተን መስራት ይገባናል ሲሉ አሳስበዋል።

ለዚህም ኢትዮጵያውያን ያላቸውን የዳበረ አብሮ የመኖር ልምድ ወደ ፖለቲከኞቻችን እና ምሁራኖቻችን በማምጣት ማዳበር እና መተግበር እንደሚገባ አቶ  ሙስጠፌ አስገንዝበዋል።

ውይይቱ ለተከታታይ ሶስት ቀናት እንደሚቆይ ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡