ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የዶናልድ ትራምፕ ፖሊሲዎችን መከለስ ጀመሩ

46ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ቃለ-መሐላ በፈፀሙ በሰዓታት ልዩነት ውስጥ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቁልፍ ፖሊሲዎችን መከለስ ጀምረዋል።

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ቃለ-መሐላ ፈፅመው ወደ ኋይት ሐውስ እንደገቡ በትዊተር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት፣ “ያጋጠሙንን ፈተናዎች ለመፍታት ምንም የምናጠፋው ጊዜ የለም” ብለዋል።

በመጀመሪያ በወሰዱት እርምጃም፣ የኮሮናቫይረስ ላስከተለው ቀውስ ምላሽ ለመስጠት የፌዴራል መንግሥቱን አቅም ያጠናክራል ያሉትን ጨምሮ 15 ፕሬዚዳንታዊ ትዕዛዞችን ፈርመዋል።

ፕሬዚዳንቱ የፈረሟቸው ሌሎች ትዕዛዞች የትራምፕ አስተዳደር በአየር ፀባይ ለውጥ እና በፍልሰት ላይ ይዞት የነበረውን አቋም የሻሩ ናቸው።

ፕሬዚዳንታዊ ትዕዛዞቹን በዝርዝር የያዘው መግለጫ፣ “ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የትራምፕ አስተዳደር የፈፀማቸውን ከፍተኛ ጥፋቶች ለመከለስ ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱን የወደ ፊት እርምጃ ለማስጀመር ጭምር ይሠራሉ” ብሏል።

በተለይ በአሜሪካ ከ400 ሺህ በላይ ሰዎችን ሕይወት የነጠቀውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለመግታት የተለያዩ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ ነው የተገለጸው። ከዚህም መካከል የፊት እና የአፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ እና አካላዊ እርቀትን መጠበቅ ግዴታ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምላሽ ለመስጠት አዲስ ቢሮ እንደሚመሠረት እና የትራምፕ አስተዳደር ከዓለም ጤና ድርጅት ለመውጣት የጀመረው ሂደት እንደሚገታም ተገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፣ አዲሱ አስተዳደር አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት ለመውጣት የምታደርገውን ሂደት ማስቆሙ የሚያስመስግነው ነው ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የአየር ፀባይ ለውጥን መግታት የአስተዳደራቸው ዋነኛ ጉዳይ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።

በአየር ፀባይ ለውጥ ላይ ያተኮረውን የ2015ቱን የፓሪስ ስምምነት ዳግም ለመቀላቀልም ፕሬዚዳንታዊ ትዕዛዝ ፈርመዋል።

ፍልሰትን በተመለከተ የትራምፕ አስተዳደር አሜሪካን ከሜክሲኮ የሚያዋስነው ድንበር ላይ ግንብ ለመገንባት ያወጣው አስቸኳይ አዋጅ በጆ ባይደን ተሽሯል።

በሌላ በኩል በአንዳንድ የሙስሊም ሀገራት ላይ በትራምፕ አስተዳደር የተጣለውን እገዳ እንዲነሳም አድርገዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።