ኅዳር 1/2015 (ዋልታ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ የሳይበር ደኅንነት ወር መከበር መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የሳይበር ደኅንነት ተጋላጭነታቸውን እንዲለዩና እንዲቀንሱ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገለጹ፡፡
“የተቀናጀ የሳይበር ደኅንነት ለሀገር ሉዓላዊነት” በሚል መሪ ቃል ከጥቅምት 1/2015 ጀምሮ የተከበረው ሦስተኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ ማስጨበጫ ወር ከዚህ ቀደም ከተከበሩ ወሮች በተሻለ መልኩ ግንዛቤ ከመፍጠርና የእውቀት ሽግግር እንዲፈጠር ከማድረግ አንፃር ስኬታማ እንደነበር ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
መርኃ ግብሩ በሳይበር ዘርፍ የተሰማሩ ተዋንያኖችን ሚና ከመጨመር ባሻገር የሰው ሃብት ልማትና የማህበረሰብ አቀፍ ግንዛቤ ፈጠራ ላይ ተመስርቶ አላማዎችን ይዞ ሲተገበር መቆየቱን አስታውቀዋል።
ሌሎች ባለድርሻዎችን ከማሳተፍና በርካታ ዝግጅቶችን ከማቅረብ እንዲሁም በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮና በማህበራዊ ድረ-ገፅ ለማህበረሰቡ ከመድረስ አንፃር ከዚህ በፊት ከተዘጋጁ ወሮች የተሻለ እንደነበር ተጠቁሟል።
የግሉን ዘርፍ ከተለያዩ የመንግስት ተቋማትና ከባለድርሻ አካላት ጋር እንዲገናኑ ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ወር እንደነበርም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
የሳይበር ወር በወርሃ ጥቅምት የሳይበር ደህንነት ማስጨበጫ የንቅናቄ መርኃ ግብር ሲሆን ወሩ በኢትዮጵያ ለሦስተኛ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ19ኛ ጊዜ ነው የተከበረው።
በሳራ ስዩም