መጋቢት 15/2013 (ዋልታ) – የሳይንስ ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ላይ በመላው ዓለም ያሉ ምሁራን በበይነ መረብ ውይይት እያካሄዱ ነው።
በዚህ የምሁራን ወይይት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈውርቅ ካሱ ምሁራን ለሀገሪቷ የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ በመሆኑ ሀገሪቱ በሳይንስ በልፅጋ ወደፊት እንድትቀጥል የራሳቸውን አሻራ እንዲያውሉ ውይይት መደረጉን ገልፀዋል።
ያደጉ ሀገራት በሳይንስ ዘርፍ ከምሁራኖቻቸው ጋር የምርምር ወጤቶች ወደ ተግባር በመግባታቸው ወጤታማ አድርጓቸዋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በዚህ መድረከ የሚሳተፋ የሳይንስ ምሁራን ጥልቅ ትንታኔ በመስጠት ለነገሮች ግልፅነትን ለመፍጠር የሚያስችል እውቀት እንዲጎለብት ያግዛል ሲሉ አንስተዋል።
በሀገሪቱ የሚካሄደው ምርምር ለአለም ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉም አክለዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቭርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወ/ሃና በበኩላቸው፣ አንጋፋው ዩኒቨርሲቲ በየዓመቱ ሁለት መቶ የምርምር ውጤቶችን እንደሚያመጣ ገልጸው፣ ለተግባራዊነቱም ጭምር እየተጋ ነው ብለዋል።
ሁሉም ዩኒቨርስቲዎች ሀገር ሊያሳድግ የሚችል የምርመር ስራዎችን ሊሰሩ ይገባል ሲሉም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የሳይንስ አካዳሚ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ፅጌ ገ/ማርያም ባቀረቡት የውይይት ሀሳብ ሳይንስን ለማበልጸግ የምርምር ወጤቶች ህዝቦቿን፣ ተፈጥሮዋን እና የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታን ማገናዘብ አለባቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የፖሊሲ ምርምር ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የሳይንስ ፖሊሲና የሰው ሀይል ልማት በኢትዮጵያ በሚል የውይይት ሀሳብ አቅርበዋል፡፡
ብቁ የሰው ሀይል መገንባት ለልማት ወሳኝ ሚና እንዳለውም ተብራርቷል፡፡
(በአካሉ ጴጥሮስ)