ሩሲያ ከአፍሪካ ጋር የምታደርገውን የልምድ ልውውጥ አጠናክራ ትቀጥላለች- ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን

መጋቢት 15 /2013 (ዋልታ) – ሩሲያ ከአፍሪካ ጋር የምታደርገውን የልምድ ልውውጥ አጠናክራ እንደምትቀጥል ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን ገለጹ።
ፕሬዘዳንት ፑቲን አፍሪካ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ለምታደርገው ርብርብም ክትባቶችን ለማቅረብ ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።
የአለም አቀፍ “ሩሲያ-አፍሪካ” ጉባዔ ግንኙነታቸውን የሚያድሱበት መድረክ ከትላንት ጀምሮ በመካሔድ ላይ ነው፡፡
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለአለም አቀፉ “ለሩሲያ-አፍሪካ” ጉባዔ ተሳታፊዎች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትን በዌብነር አስተላልፈዋል።
በአጀንዳው ሰላምን ማስፈን፣ የቀጠናዊ ደህንነትን ማረጋገጥ እንዲሁም በሉዓላዊ ሃገራት ጣልቃ ገብነትን መከላከል የሚሉ ነጥቦች ተካተውበታል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ኢኮኖሚያዊ እድገትን ማጠናከር እና የሰብአዊ መብቶች ትስስር የሚሉ ነጥቦችም በአጀንዳው ተካተዋል፡፡
የኮቪድ-19 ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ለሚደረጉ ጥረቶች ሩሲያ ክትባቶችን ማቅረብን ጨምሮ ሌሎች ወሳኝ ሚና እንደምትጫወት ተገልጿል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን ሩሲያ በዘርፉ የተከማቸ ልምዷን ማካፈሏን አጠናክራ እንደምትቀጠል ተናግረዋል።
በፈረንጆች የዘመን ቀመር በ2019 የተካሄደው የመጀመሪያው የሩሲያ እና የአፍሪካ ጉባዔ በአገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማዳበር የሚያስችል ጉልበት እንደሆነ በኢትዮጵያ የሩሲያ ኢምባሲ ገልጿል፡፡
የአሁኑ ኮንፈረንስ በ 2022 ለታቀደው ለሁለተኛው የሩሲያ እና አፍሪካ ጉባዔ ዝግጅት አንዱ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል ፕሬዚዳንት በመልዕክታቸው፡፡