የሴካፋ ውድድር የምድብ ድልድል ይፋ ሆነ

መስከረም 22/2015 (ዋልታ) በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ከነገ ጀምሮ የሚካሄደው ከ17 ዓመት በታች የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት (ሴካፋ) እግር ኳስ ውድድር የምድብ ድልድል ይፋ ሆኗል።
በዚህም በምድብ አንድ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያና ታንዛንያ፤ በምድብ ሁለት ዩጋንዳ፣ ቡሩንዲና ደቡብ ሱዳን ተደልድለዋል።
ነገ በውድድሩ መክፈቻ ዕለት ከቀኑ 7 ሰዓት ዩጋንዳ ከቡሩንዲ እንዲሁም ከቀኑ 10 ሰዓት ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ይጫወታሉ።
ውድድሩ ከመስከረም 21 እስከ ጥቅምት 9 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚካሄድ ቀን ተቆርጦለት የነበረ ቢሆንም በውድድሩ ይሳተፋሉ ተብሎ የሚጠበቁ 4 ብሔራዊ ቡድኖች በተለያየ ምክንያት ባለመሳተፋቸው ቀድሞ የወጣው የምድብ ድልድል በድጋሚ እጣ ወጥቶ ከነገ ጀምሮ በስድስት አገራት መካከል ውድድሩ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ገልጿል።
የሴካፋ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር ከመስከረም 23 እስከ ጥቅምት 5 ቀን 2015 ዓ.ም በአበበ ቢቂላ ስታዲየም እንደሚካሄድ የፌዴሬሽኑ መረጃ አመላክቷል።