የሽግግር ፍትሕ ለኢትዮጵያ ችግሮች እንዴት መፍትሔ ይሆናል?

በብርሃኑ አበራ

የሽግግር ፍትሕ ምንድን ነው?

የሽግግር ፍትሕ ለተጎጂዎች እውቅና ለመስጠት፣ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የግለሰቦችን አመኔታ ለማሳደግ፣ የሰብዓዊ መብት መከበርን ለማረጋገጥ እና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር እንዲሁም በሕዝቦች መካከል እርቅ ለመፍጠር አስፈላጊ መሆኑ ይታመናል፡፡

ዘላቂ ሰላምና የሕግ የበላይነት እንዲኖር ማድረግ፣ በመደበኛ ሕግ መፍታት የማይቻሉ የቆዩ ችግሮች ለመፍታት እና ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ለማድረግ የሽግግር ፍትሕ ሁነኛ መሳሪያ ነው፡፡ በግጭት ውስጥ ባለፈች አንዲት ሀገር የተፈጸሙ ጥሰቶችን ለማጥራት እና እርቅ ለመፍጠር እጅግ ጠቃሚ መሆኑም ይነገራል፡፡

የሽግግር ፍትሕ በኢትዮጵያ ለምን ያስፈልጋል?

በሕዝቦች መካከል መተማመን እና ዘላቂ ሰላምን ለመፍጠር ሁሉንም የሚያሳትፍ፣ የሕግ ተጠያቂነት፣ ፍትሕ፣ እርቅና ካሳን ጭምር ታሳቢ የሚያደርግ ብሔራዊ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ በኢትዮጵያ ለመተግበር ታቅዶ እየተሠራ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማዕቀፍ መዘርጋት አስፈላጊነት ታምኖበት ሁሉን አቀፍ አካታችና ተመጋጋቢ የሆነ ፖሊሲ ለማዘጋጀት ባለፉት ወራት የግብዓት ማሰባሰቢያ የውይይት መድረኮች ሲካሄዱ ቆይተዋል፡፡

በሀገሪቱ ያሉ ግጭቶችን ለመፍታትም ሀቅንና እርቅን በማመቻቸትና ተጠያቂነትን በማስፈን መፍትሄ ማፈላለግ ሰላምን የመፍጠሪያ አንድ አማራጭ በመሆኑ ለኢትዮጵያ አሁናዊ ሁኔታ አስፈላጊ መሆኑን የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች ቡድን አባል ማርሸት ታደሰ (ዶ/ር) ለአዲስ ዋልታ ዲጂታል ሚዲያ ገልጸዋል፡፡

ግጭትን በዘላቂነት ለመፍታት፣ በሕዝቦች መካከል መተማመንን ለመፍጠር፣ በጦርነት ወቅት ለተከሰቱ የመብት ጥሰቶች እና ወንጀሎች ምላሽ በመስጠት ረገድ እንዲሁም ከልዩነት ትርክቶች እና ቁርሾዎች ለመውጣት ፍትሕን ማስፈን እና እርቅን ማምጣት አስፈላጊ በመሆኑ የሽግግር ፍትሕን እውን ለማድረግ አማራጭ ፖሊሲ አፈላላጊ ቡድን ተዋቅሮ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል፡፡ በዚህም የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች ቡድን በርካታ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች ቡድን ባለፉት ዘጠኝ ወራት ምን ምን ሰራ?

14 አባላት ያሉት የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች ቡድን ባለፉት ዘጠኝ ወራት በርካታ ስራዎች ማከናወኑን በሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ከፍሎ አስቀምጧቸዋል፡፡

የሽግግር ፍትህ አስፈላጊነት እና ወቅታዊነት፣ የሽግግር ሥርዓት ህዝባዊ ምክክር እና የፖሊሲ ቀረጻ ሂደቱ አሁን ስላለበት ደረጃ እንዲሁም እየተወሰዱ ስለሚገኙ እርምጃዎች፣ የሽግግር ፍትህ እና ሀገራዊ የምክክር መድረኮች ያላቸው ተመጋጋቢነት እና ልዩነቶች አንኳር ነጥቦች ናቸው፡፡

በዋናነት ለውይይት የሚሆን የፖሊሲ አማራጭ ሃሳብ መሰነድ፣ ሃሳብ ማሰባሰብ፣ ውይይት ማካሄድና የተገኙ ግብዓቶችን ማደራጀት ወይም መፃፍ እንዲሁም ሀገራዊ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ዋና ዋና ክንውኖች እንደነበሩ ተጠቁሟል፡፡

የሽግግር ፍትሕ ምን አዲስ ነገር ይዞ መጣ?

የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ቡድን አስተባባሪ ታደሰ ካሳ (ዶ/ር) የሽግግር ፍትህ ፖሊሲው ዝግጅት በኢትዮጵያ የህግና የፖሊሲ አወጣጥ ታሪክ ያልተለመደና አዲስ ነገርን ይዞ የመጣ መሆኑን ጠቁመው ከላይ ወደታች የነበረውን የፖሊሲ አወጣጥ በማስቀረት ከታች ወደላይ አሰራርን የተከተለና ለህዝቡ ሰፊ እድል የሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም በመንግስት በኩል ሀገርና ህዝብ የሚፈልጉትን ነገር አንጥሮ ለመለየት እድል የሰጠ፣ ህብረተሰቡ በትግበራው ላይ የሚኖረውን ቁርጠኝነት የተሻለ ለማድረግና ወሳኝ የሆኑ የአካታችነት፣ የግልጽነት፣ የገለልተኝነትና ሌሎች መርሆዎችን በተሻለ መልኩ ለመተግበር እድል የሚሰጥ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የሽግግር ፖሊሲ አማራጮች ላይ ውይይት በማካሄድ ሃሳብ ሲቀርብ መቆየቱንም የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች ቡድን አባል ማርሸት ታደሰ (ዶ/ር) ይገልጻሉ፡፡

እስካሁን በየትኞቹ አካባቢዎች ውይይቶች ተደርገዋል?

በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም በ12 ክልሎች በጥቅሉ በ59 አካባቢዎች ውይይቶች የተደረጉ ሲሆን ከ40 ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ከ200 በላይ የህግ መምህራን በሂደቱ ተሳታፊ መሆናቸውን የቡድኑ አስተባባሪ ታደሰ ካሳ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡

የቀጣይ የቡድኑ ተግባር ምንድን ነው?

በእነዚህ መድረኮች የተሰባሰቡ ግብዓቶችን ማደራጀትና መተንተን፣ ዋና ዋና ግኝቶች ላይ የማጠቃለያ ሪፖርት ማዘጋጀትና በመጨረሻም ብሄራዊ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማዕቀፍ አዘጋጅቶ ማስረከብ የቀጣይ የቡድኑ ተግባራት መሆናቸው ተብራርቷል፡፡

የሽግግር ፍትሕ ከሀገራዊ ምክክር ጋር ያለው ተመጋጋቢነት እና ልዩነት ምንድን ነው?

የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች ቡድን አባል ምስጋናው ሙሉጌታ ልዩነትና ተመጋጋቢነትን አስመልክቶ ሲያብራሩ ውስብስብና መጠነ ሰፊ ችግር ባለባቸው ሀገራት ከነዚህ አማራጮች በዘለለ ሌሎች ሂደቶችም በአንድ ላይ እንደሚተገበሩና ሀገራዊ ምክክርና የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲዎችም ተመጋጋቢና ነገር ግን የተለያዩ አውድና ግብ ያላቸው ሂደቶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ሁለቱም ለዘላቂ ሰላምና ለአገረ መንግስት ግንባታ የራሳቸው መሰረታዊ አስተዋፅኦ እንዳላቸውና የሽግግር ፍትሕ ዋነኛው ትኩረት ተፈፀሙ የሚባሉ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ላይ መሆኑንና በእነዚህ ሂደቶች ክስ የሚኖር መሆኑን በመግለፅ በሀገራዊ ምክክር ላይ ግን በአብዛኛው ክስ የሌለ መሆኑ ልዩ ያደርጋቸዋል ብለዋል፡፡

የሽግግር ፍትሕ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ምን ይመስላሉ?

የተለያዩ ሀገራት የሽግግር ፍትሕን ተግባራዊ አድርገው እውነትን አፈላልገው፣ የተጎዱ ሰዎችን ክሰው፣ ለወንጀለኞች ፍርድ ሰጥተው እንደ ሀገር ቀጥለዋል፡፡

ለዚህም እንደ ምሳሌ ደቡብ አፍሪካ፣ ሴራሊዮን፣ ላይቤሪያ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ጋምቢያ፣ ሩዋንዳ፣ ዩጎዝላቪያ፣ ቺሊ እንዲሁም ሌሎች በርካታ ሀገራትን ተሞክሮ መጥቀስ ይቻላል፡፡

በተጨማሪም በዩጎዝላቪያ፣ ቺሊ፣ ጋምቢያ እና ሌሎች ሀጋራት ላይ ተበዳዮች የተካሱበት አጥፊዎች በሂደቱ ፍርድ ያገኙበት ሁኔታ ተፈጥሯል። እንደ ማሳያ ከላይ የተጠቀሱትን ሀገራት አነሳን እንጂ በርካታ የዓለም ሀገራት ዘላቂ ሰላም፣ ፍትሕና ዕርቅን ለመፍጠር ሂደቱን ተጠቅመውበታል፡፡

የሽግግር ፍትሕ በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ሲተገበር ምን ይጠበቃል?

የሽግግር ፍትሕ በአግባቡ ሲተገበር ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ የተሻለ ነገን መፍጠር የሚችል ሲሆን ትኩረቱን ልማት ላይ የሚያደርግ እና ቅራኔ የሌለው ማኅበረሰብ ለመፍጠር ያስችላል፡፡ ሂደቱን ከተገበሩ ሌሎች ሀገራት የተስተዋለውም ውጤት ይህንኑ ያረጋግጣል፡፡

የሽግግር ፍትሕ ትግበራው ውጤታማ እንዲሆን ከማን ምን ይጠበቃል?

በሽግግር ፍትሕ ወቅት ለታሰበው ተልዕኮ ውጤታማነት የምሁራን፣ የሚዲያ እንዲሁም የኅብረተሰቡ ሚና ከምንጊዜውም በላይ አስፈላጊ በመሆኑ ሁሉም የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በመተግበር ሀገራዊ ግዴታውን ሊወጣ እንደሚገባ የሽግግር ፍትሕ ባለሙያዎች ቡድን አሳስቧል፡፡