ማገልገል መገልገል!

የምንኖረው በራሳችን ፍላጎቶች እና ምኞቶች ላይ እንድናተኩር በሚያበረታታ አለም ውስጥ ነው። ያለነው በራስ ጥቅም በተተበተበ ዓለም ውስጥ ነው፡፡ የሚሻለን አንድ ላይ ተሰባስበን የተሻለ ህዝብና ሃገርን መገንባት ነው። አላማችን ጊዜያችንን፣ ችሎታችንን እና ኃብታችንን ለመልካም ነገር ማዋል ነው።

 

ትኩረታችንን ከራሳችን ወደ ሌሎች ስንቀይር የርኅራኄ፣ የመተሳሰብ እና የደግነት ምንጭ ውስጥ እንሆናለን። ሌሎችን በማገልገል እውነተኛ ማንነታችንን እናገኛለን። ህይወታችን ከግል ፍላጎታችን በላይ አላማ እንዳለው እንገነዘባለን።

 

ማገልገል መገልገል ነው፤ የመስጠት ተግባር እርስ በእርስ የሚደጋገፍ ነው። ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንን እና ችሎታችንን ለሌሎች ስንሰጥ በምላሹ የበለጠ ጠቃሚ ነገር እናገኛለን። በማናቸውም ቁሳዊ ንብረት ወይም ግላዊ ስኬት ውስጥ የማይገኝ እርካታ፣ ትርጉም እና ዓላማን እናገኛለን። ሌሎችን በማገልገል የምናገኘው ደስታ ዘላቂ እና ጥልቅ ነው።

ሌሎችን በማገልገል ለግል እድገትና ስኬት አስፈላጊ የሆኑትን ባሕርያት እናዳብራለን። ከራሳችን የሚበልጥ ነገር አካል መሆናችንን ስንገነዘብ ትህትናን እንሸምታለን። በሕይወታችን ውስጥ ላሉት በረከቶች የበለጠ አመስጋኞች ስንሆን ምስጋናን እናሳድጋለን። ሌሎች የሚያጋጥሟቸውን ትግሎች እና ተግዳሮቶች ጠለቅ ብለን ስንረዳ ርህራሄን እንታጠቃለን። እንቅፋቶችን ማሸነፍን እና በችግር ጊዜ መጽናትን ስንማር ጽናትን እንገነባለን።

 

ለውጥ ማምጣት የምንችልባቸውን መንገዶች የምናሳይበት እና የተቸገሩትን ለመርዳት እርምጃ የምንወስድበት ቀን ነው። ዛሬ፣ አገልግሎትን የምናከብርበት ቀን ነው።

የሰው ልጅ እውነተኛው ማንነት የተመሰረተው አንዳችን ሌላችንን ከፍ ለማድረግ፣ የእርዳታ እጃችንን ለመዘርጋት እና በዙሪያችን ባሉ ሰዎች ህይወት ላይ በጎ ተጽእኖን ለመፍጠር ባለን አቅም ላይ ነው።

 

አገልግሎት ጫና አይደለም፡፡ ከዚያ ይልቅ ለውጥ ለመፍጠር የሚያስችለን ትልቅ እድል ነው። ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ ለሌሎች ስናገለግል፣ ፍሬ የሚያፈሩ የተስፋ ዘሮችን እንተክላለን። ማንኛውም የአገልግሎት ተግባር ምንም ያህል ትንሽ ቢሆን እንኳን ማህበረሰባችንን ወደ ሽቅብ እድገት ለሚወስደው የጋራ ተነሳሽነት አስተዋፅዖ ያደርጋል።

 

በአገልግሎት ተግባራቸው ታሪክን የፈጠሩ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ያልተዘመረላቸው ጀግኖችን እናስብ። በተማሪ አእምሮ ውስጥ የማወቅ ጉጉትን የሚያቀጣጥሉ መምህራን፣ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ህክምና የሚሰጡ የጤና ባለሙያዎች፣ ለማህበረሰባችን በችግር ጊዜ ደራሽ  የሆኑ በጎ ፈቃደኞችን እናስብ። ትናንሽ የሚመስሉን የአገልግሎት ተግባሮቻቸው ህይወትን የመለወጥ፣ እጣ ፈንታን የመፃፍ እና የወደፊት ብሩህ ተስፋን ዘር የመዝራት ሃይል እንዳላቸው ያስታውሱናል።

 

አገልግሎት ትላልቅ ነገሮችን በማከናወን ብቻ የተገደበ እንዳልሆነ መዘንጋት የለብንም። በየእለቱ በምናደርጋቸው ትንንሽ ምርጫዎች ውስጥ ይኖራል፡፡ ድርጊቱ ምንም ያህል ትልቅም ይሁን ትንሽ፣ እያንዳንዱ የአገልግሎት ተግባር ለውጥ ያመጣል። ለሌሎች እንደምንጨነቅ እና የተቸገሩትን ለመርዳት ፈቃደኛ መሆናችንን ለአለም ያሳያል።

አገልግሎት ለማያውቀን ሰው በምንናሳየው ፈገግታ፣ በጭንቀት ውስጥ ላለ ጓደኛችን በምንሰጠው ጊዜ፣ ከጎረቤታችን ጋር ባለን መልካም ጉርብትና እና ህይወት ላላቸው ፍጥረታት በምንሰጠው ርህራሄ ውስጥ ይገኛል። አገልግሎት በእያንዳንዳችን ውስጥ ያለ ገደብ የለሽ ፍቅር ማሳያ ነው፡፡

 

ይህንን የአገልጋይነት ቀን ስናከብር በውስጣችን ስላለው ለውጥ የመፍጠር አቅም እናስብ። ርህራሄ እና ልግስና የበለፀገችበት አለም መሀንዲሶች የመሆን፣ የለውጥ ወኪሎች የመሆን ቃላችንን እናድስ። እያንዳንዱ የአገልግሎት ተግባር መጠኑ ምንም ይሁን ምን የሕብረተሰባችንን ስብራት ሊጠግን የሚችል የአንድነት ማሳያ እንደሆነ እናስታውስ።

 

መንገዳችን ማገልገል ይሁን፡፡ የአገልግሎት መንገዱ ወደፊት ይጠቁመናል፣ ማየት የምንፈልገው ለውጥ እንድንሆን ያሳስበናል። ስለዚህ ይህንን መንገድ በቀና ልብ እና በቆራጥ መንፈስ እንቀበለው። በዚህ የተከበረ ጉዞ ላይ ሌሎችን በማነሳሳት በአርአያነት እንምራ።

 

አገልግሎት ኩነት ብቻ ሳይሆን የህይወት መንገድ መሆኑን እናስታውስ። የማህበረሰባችን የመሠረት ድንጋይ፣ የጋራ ሰብአዊነታችን መገለጫ እና ለትውልድ የምንተወው ትሩፋት ነው። በዚህ የአገልግሎት ቀን ሁላችንም ሌሎችን ለማገልገል ራሳችንን እንስጥ። ዛሬ ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ ቀናችን የአገልግሎትን ነበልባል ሳይጠፋ ለማቆየት ቃል እንግባ። መገልገልን በማገልገል እናጽና።

 

በቴዎድሮስ ኮሬ