ሃገራችን ካለችበት አሁናዊ ሁኔታ አንፃር ከመቼውም ጊዜ በላይ የቀደሙ አባቶቻችን የአርበኝነት ወኔ እና አበርክቶ በዚህ ትውልድ መድገም እንደሚጠበቅ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡
ሚኒስትሩ ለ80ኛ ዓመት የአርበኞች የድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አሁን የገባንበት ትግል ሃገር ለማፍረስ እና ሃገር ለማቆም በሚደክሙ ሃይላት መካከል የሚካሄድ በመሆኑ፤ አፍራሽ ሃይሎች አቅም እና ጊዜ እንዳይገዙ ትውልዱ ሃገርን በማዳን ተልእኮ ውስጥ የአርበኝነት ሚናውን ሊወጣ ይገባልም ሲሉ አሳስበዋል።
ከውስጥ እና ከውጭ የተደቀኑብንን ፈተናዎች በድል እና በስኬት ለመሻገር፤ የውስጥ ልዩነቶቻችን ወደኋላ ሳይጎትቱን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት እና በጋራ ሊቆም እንደሚገባም ምክትል ጠቅላይሚኒስትሩ ገልጸዋል።
”የኢትዮጵያ ውስጣዊ አንድነት መጠናከር የክብራችን ምንጭ እና የኩራታችን ጥግ መሆኑን በውል በመረዳት፤ በሁሉም የለውጥ እና የእድገት መስመሮች እያበርን ኢትዮጵያን ማሻገር ይጠበቅብናልም” ብለዋል በመልዕክታቸው።
”ሁላችንም እንደምንገነዘበው እስካሁን አንድነታችን ፀንቶ በማበራችን በርካታ መሰናክሎችን ተሻግረናል፤ በቀጣይ ህብረታችን ጠብቆ ትውልድ እና ሃገር በሚያሻግሩ ተግባራት ላይ እንድንረባረብ አደራ ለማለት እወዳለሁ” ማለታቸውን ከማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።