የቀድሞው የሊቨርፑል አሰልጣኝ ጄራርድ ሁዬ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

የቀድሞው የሊቨርፑል አሰልጣኝ ጄራርድ ሁዬ በ73 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

ፈረንሳዊው አሰልጣኝ ጄራርድ ሁዬ ሊቨርፑልን ከፈረንጆቹ 1998 እስከ 2004 ድረስ በአሰልጣኝነት መርተውታል።

በሊቨርፑል በነበራቸው ቆይታም የኤፍ ኤ ካፕ፣ የሊግ እና በቀድሞው ስያሜው የአውሮፓ ማህበረሰብ ዋንጫ በአሁን መጠሪያው ዩሮፓ ሊግ ዋንጫዎችን ጨምሮ አምስት ዋንጫዎችን ከቡድኑ ጋር አንስተዋል።

ጄራርድ ሁዬ ከሊቨርፑል ባሻገር ሌንስ፣ ፓሪስ ሴንትጀርመን፣ የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድንን እና ሊዮንን በአሰልጣኝነት መርተዋል።

በመጨረሻ አስቶንቪላን በአሰልጣኝነት የመሩ ሲሆን በ2011 ከልብ ህመም ጋር ተያይዞ ከዘጠኝ ወራት በኋላ ከክለቡ ጋር መለያየታቸውን ቢቢሲ በዘገባው ላይ አስፍሯል።

ሊቨርፑል ባወጣው የሀዘን መግለጫ በቀድሞ አሰልጣኝ  ጄራርድ ሁዬ ህልፈት በጥልቁ አዝነናል ብሏል።