የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የነበሩት ዘውዴ ተክሉ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የነበሩት ዘውዴ ተክሉ

ሐምሌ 12/2013 (ዋልታ) – የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የነበሩት ዘውዴ ተክሉ በተወለዱ በ85 ዓመታቸው በትላትናው ዕለት ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ተገልጿል።

የከንቲባ ዘውዴ ተክሉ የቀብር ሥነ-ሥርዓት በነገው ዕለት በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ከቀኑ በ6:30 የሚፈጸም መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕሬስ ሴክሬተሪያት ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ከረፋዱ 4:00 ሰዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቅጥር ግቢ /ማዘጋጃ ቤት/ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ የፌዴራል እና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች፣ ወዳጅ ዘመድ እና ቤተሰቦቻቸው በሚገኙበት የአስከሬን ሽኝት ፕሮግራም የሚከናወን መሆኑም ተገልጿል።

ከንቲባ ዘውዴ ተክሉ በ1973 ዓ.ም በተደረገው 3ኛ ዙር የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ማኅበራት ምርጫ ከንቲባ በመሆን ተመርጠው ከ1973 እስከ 1981 ዓ.ም ድረስ በከንቲባነት አገልግለዋል።