የቃላት ሻሞላ ማማዘዝ የጀመረው የአሜሪካ ምርጫ

የቃላት ሻሞላ ማማዘዝ የጀመረው የአሜሪካ ምርጫ

በመንገሻ አለሙ

ከዋናው ቀን ይልቅ ሂደቱ አብዝቶ የዓለምን ቀልብ የሚስበው የአሜሪካ ምርጫ በቀድሞውና በወቅቱ ፕሬዝዳንቶች መካከል ከወዲሁ የቃላት ሻሞላ ማማዘዝ ጀምሯል፡፡

በተገኙበት መድረክ ሁሉ ውዝግብ የማያጣቸው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከአንድ ወር በፊት ከደጋፊዎቻቸው ጋር በተገናኙበት ወቅት ዲሞክራቶቹን እነዚህ አሜሪካን ያቀጨጩ አረሞችን ነቅለን ከነጩ ቤት እናስወጣቸዋለን ሲሉ ዝተዋል፡፡

በየክርክር መድረኩ ብሽሽቅ የሚቀናቸው ትራምፕ ተቀናቃኖቻቸውን ዲሞክራቶች ኮሚኒስቶች፣ ማርክሲስቶች፣ ፋሺስቶችና አክራሪ ግራ ዘመሞች በማለት ነው የሚብጠለጥሏቸው፡፡ ትራምፕ እንደ አብዛኞቹ የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ሁለት የምርጫ ጊዜዎችን በዋይት ሃውስ እንዳይቆዩ ያደረጓቸውን ጆ ባይደንን ለመበቀል ቆርጠው የተነሱ ይመስላሉ፡፡

ለወትሮው እንደተቀናቃኛቸው ትራምፕ እላፊ ቃላትን በመናገር ብዙ የማይታወቁት ጆ ባይደንም በቦስተን ከደጋፊዎቻቸው ጋር በነበራቸው የገንዘብ ማሰባሰቢያ መርኃ ግብር ላይ ለትራምፕ ምላሽ ይሆናል ያሉትን በተንኳሽ ቃላት የታጀበ ንግግር አድርገዋል፡፡

እርግጠኛ ሆኘ ልነግራችሁ የምፈልገው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዳግም ወደ ስልጣን እንዲመጣ የማሸነፍ እድል እንደማንሰጠው እንድታውቁ ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ አክለውም ተቀናቃኛቸውን ለማናደድ ይረዳኛል ያሉትን ሀሳብ ሲናገሩ እንዲያውም አንድ ነገር ልንገራችሁ፤ ትራምፕ በ2024ቱ ምርጫ ለመወዳደር ባይወስኑ ኖሮ ለሁለተኛ ጊዜ ለመፎካከር እግሬን አላናሳም ነበር የመጣሁት እሱን ለማሸነፍ ነው ብለዋል፡፡

ይህ የፕሬዝዳንት ባይደን አስተያየት የተሰማው የሪፐብሊካን ፓርቲ እጩና ግንባር ቀደም ተፎካካሪ የሆኑት ዶናልድ ትራምፕ ዲሞክራትን የአሜሪካ ጠላት ብለው ከፈርጇቸው በኋላ ነው። ትራምፕ በአሁኑ ወቅት ለሁለተኛው ተርም የዋይት ሀውስ ቆይታቸው ለመፎካከር እቅስቃስቃሴ የጀመሩትን ባይደን/ ከዚህ በኋላ ሀገር ለመምራት ዕድሜው አይፈቅድለትም፤ አርፎ ጡረታ ይውጣ ሲሉ የተለመደውን የቃላት ጦርነት አልመው ተኩሰዋል፡፡

ይሁን እንጂ ትራምፕ በሆነ አጋጣሚ ምርጫውን ጥለው ቢወጡ እርሶም ይተውታል ወይ የሚል ጥያቄ ከጋዜጠኞች ሲቀርብላቸው አይ አሁንማ አንዴ ጀምሬዋለሁ ወደኋላ የለም በማለት ከቃላቸው ሲያፈገፍጉ መታየታቸውን ስካይ ኒውስ ዘግቧል፡፡

አንጋፋው የፎክስ ኒውስ ዘጋቢ ሲያን ሃኒቲ ደግሞ ዶናልድ ትራምፕን በምርጫው እድል ቢቀናዎትና ቢያሸንፉ ስልጣንዎን ያለ አግባብ በመጠቀም ይቀብጡ ይሆን የሚል ጥያቄ ጠይቋቸው ነበር፡፡ ስራ በምገባበት በመጀመሪያው ቀን አዎ ካሉ በኋላ ከዚያ ቀጥሎ በሚኖረኝ ቆይታዬ ግን በፍጹም አምባገነን አልሆንም፤ በመጭው ምርጫ ከሸነፍኩ ባይደንን ችሎት እንደማቆማቸው ግን አትጠራጠሩ ብለዋል፡፡

ከአሁን ቀደም ከሂላሪ ክሊንተን ጋር ሲፎካከሩም ይህንኑ ቃል ተናግረውት ነበር፡፡ ሂላሪ ክርክራቸውን ጨርሰው ወደ መመቀማጫቸው ሲመለሱ ትራምፕ ጣታቸውን ወደሳቸው እየጠቆሙ እኔ ስመረጥ የመጀመሪያ ስራዬ የሚሆነው አንችን እስር ቤት ማስገባት ነው፤ ይህንንም በመሃላ አረጋግጥልሻለሁ ነበር ያሏቸው፡፡

የትራምፕን ንግግር የሰሙ ዘ ዋሽንግተን ፖስት፣ ዘ አትላንቲክና ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ የተባሉት ጋዜጦች ከመቅጽበት አምባገነኑ ትራምፕ አሁንም ለዴሞክራሲ ስጋት ናችው ሲሉ በፊት ገጾቻቸው ጽፈዋል፡፡

ጋዜጠኛው ሃኒቲ ትራምፕን በቀላሉ ሊተዋቸው አልፈለገምና ስልጣንዎን ተገን አድርገው ህግ ለመጣስ ይሞክራሉ ወይ የሚል ሌል ጥያቄ ጠየቃቸው፡፡ እሳቸውም የዋዛ አይደሉምና ፈጠን ብለው አሁን ስልጣን ላይ ያሉት ሰዎች እንደሚያደርጉት ማለትህ ነው? ሲሉ ቀስቱን ወደተፎካካሪያቸው ሲያዞሩት ታይተዋል፡፡

ተፎካካሪዎች ለደጋፊዎቻቸው ዓላማቸውን ሲያስረዱ ትራምፕ አሜሪካን ዳግም ታላቅ ማድረግ ሲሉ ባይደን ደግሞ የሀገራችንን ነፍስ ለመመለስ እንሰራለን ይላሉ፡፡ ትራምፕ ዴሞክራቶቹ አሜሪካን የሽብርተኞች መፈንጫ አድርገዋታል፤ ህዝቡን ከየትኛውም ጥቃትና ውርደት ለመጠበቅ አቅመ ቢሶች ናቸው የሚል ጠንካራ ትችት ሲያቀርቡ፤ ባይደንና የፓርቲ ጓዶቻቸው ደግሞ ሀገራችን በዘመነ ትራምፕ የደረሰባትን ያህል የዲፕሎማሲ ኪሳራ መቼም አጋጥሟት አያውቅም፣ ሰውየው ከንግድ ተነስተው በማያውቁት ፖለቲካ ዘው ብለው ገብተው አንገታችንን አስደፍተውናል በማለት ይከሷቸዋል፡፡

ይሁን እንጂ የአሜሪካ ህዝብ ሁለቱንም መሪዎች የአራት ዓመት የዋይት ሀውስ ቆይታቸውን በሚገባ ታዝቧል፡፡ እናም ማን የተሻለ እንደሆነ አመዛዝኖ በድምጹ ብይን ለመስጠት መጭውን ምርጫ በትዕግስት መጠበቅ ግድ ይላል፡፡
የመረጃው ምንጭ ሲ ኤን ኤን፣ ቢቢሲ፣ ስካይ ኒውስና ሞርኒንግ ስታር ነው።