የቆዳ ኢንዱስትሪው ዘርፍ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆን ይሰራል- አቶ መላኩ አለበል

መጋቢት 15/2013 (ዋልታ) – የቆዳ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከተጋረጠበት ችግር ተላቆ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆን ከፍተኛ ድጋፍና ክትትል ይደረጋል ሲሉ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ።

በበጀት አመቱ የ8 ወራት በቆዳ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰሩ ተግባራት፣ ያጋጠሙ ችግሮችና በቀጣይ በሚሰሩ ስራዎች ዙሪያ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብት በአፍሪካም ሆነ በዓለም ደረጃ ከቀዳሚዎቹ ተርታ ያስቀምጣታል።

ይሁን እንጂ ባለፈው አመት ከኤክስፖርት ብቻ ከዘርፉ የተገኘው ገቢ 3 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ሲሆን፣ በደንብ ከሰራን ሀገሪቱ ገቢውን ወደ 3 ቢሊየን ማሳደግ የሚያስችል አቅም እንዳላት ገልጸዋል፡፡

በሀገሪቱ ወደ 29 የሚደርሱ የቆዳ ኢንዱስትሪዎች ቢኖሩም በሙሉ አቅማቸው እየሰሩ የሚገኙት ውስን መሆናቸውም ጠቁመዋል።

በተለይም የማምረቻ ቦታ እጥረት፣ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ፣ የብድር እጥረት፣ የጥሬ እቃ እጥረት፣ የጥራት ጉድለቶች የሴክተሩ ፈተናዎች በመሆናቸው ዘርፉን ከነዚህ ችግሮች በማላቀቅ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆን ይሰራል ብለዋል።

የቆዳ ኢንዱስትሪዎች ከስራ እድል ፈጠራ ባሻገር በአመት እስከ 400 ሚሊየን ዶላር ግብይት የሚፈፀምበት በመሆኑ፤ ተጨማሪ አቅም ለመፍጠር ሜኒስቴሩ ድጋፍ እንደሚያደርገውም ተናግረዋል።

(በደረሰ አማረ)