መጋቢት 27/2013 (ዋልታ) – የቡልቡላ የተቀናጀ የግብርና ማቀነባበሪያ ፓርክ በሚያዚያ ወር መጨረሻ ይመረቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ የንግድ እና ኢነዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የሚኒስቴሩ ከፍተኛ አመራሮች ፓርኩን የጎበኙ ሲሆን፣ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል የፓርኩ አጠቃላይ የግንባታ ምዕራፍ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልፀው፣ ያላለቁ መሰረተ-ልማቶች በእሰቸኳይ እንዲጠናቀቁ አሳስበዋል፡፡
ፓርኩን ማስመረቅ ብቻ ትርጉም እንደሌለው የተናገሩት አቶ መላኩ፣ ይልቁንም ፓርኩን ለባለሃብቶች ምቹ ማድረግ ከምንም በላይ ልዩ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉት በሚኒስቴሩ የአግሮ-ፕሮሰሲንግና ፋርማሲዩቲካል ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተካ ገ/የስ የፓርኩ አጠቃላይ የግንባታ ሂደት መልካም እንደሆነና የፓርኩን የመሠረተ-ልማት የግንባታ ሂደት በተለይም የሃይል አቅርቦት ዝርጋታን በተመለከተ ሚኒስቴሩ ከሚመለከተው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል የተቀናጀ የግብርና ማቀነባበሪያ ፓርኮች አስተባባሪ አቶ ሲሳይ ገመቹ በበኩላቸው፣ የፓርኩ መገንባት እና ወደ ስራ መግባት ለክልሉ ዜጎች የስራ ዕድልን በመፍጠር ረገድ ሚናው የላቀ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በርካታ ባላሃብቶች ወደ ፓርኩ ለመግባት ከፍተኛ ፍላጎት ቢያሳዩም የመሠረተ-ልማት ግንባታ ሂደት አለመጠናቀቁ ባለሃብቶች ወደ ፓርኩ እንዳይገቡ ትልቅ ተግዳሮት መሆኑን ተናግረው፣ የክልሉ መንግስት ከሚያደርገው ጥረት በተጓዳኝ ሚኒስቴሩ የጉዳዩን አንገብጋቢነት ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት እልባት እንዲሰጠው መጠየቃቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡