የቡራዩ ከተማ አስተዳደር በበጀት አመቱ ከፍተኛ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የሴክተር መ/ቤቶችን እውቅና ሰጠ

ሐምሌ 25/2013 (ዋልታ) – የቡሪዩ ከተማ አስተዳደር የ2013 ዓ.ም የበጀት አመት የስራ ግምገማ አካሄዷል።
በግምገማው ላይ ባለፈው በጀት አመት ከፍተኛ አፈፃፀም ላስመዘገቡ ተቋማት እና ሴክተር መስሪያ ቤቶች እውቅና እና ሽልማት ሰጥቷል።
ከተማዋ ለመኖሪያ ምቹ ፣ ሰላሟ የተጠበቀ እና ልማቷ የተረጋገጠ እንድትሆን የራሳቸውን አስተዋፅኦ ያበረከቱ 3 ሴክተር መስሪያ ቤቶች፣ መልካም አስተዳደርን ያረጋገጡ የከተማዋ 3 ቀበሌዋች ተሸላሚ ሆነዋል።
በሽልማት ስነስርአቱ ላይ ከ6 የከተማዋ ቀበሌዎች የላቀ አፈፃፀም ያስመዘገቡ የቡራዩ ከተማ ገፈርሳ ቀበሌ በሶስተኛ ደረጃ ፣ ገፈርሳ ጎጄ ቀበሌ በሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም መልካ ገፈርሳ በ2013 ዓ.ም በላቀ አፈፃፀም በአንደኝነት የዋንጫ ተሸላሚ ሆነዋል።
በቡራዩ ከተማ 27 ሴክተር መስሪያ ቤቶች የሚገኙ ሲሆን የገቢዎች መ/ቤት በአንደኛ ደረጃ፣ የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት በሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም የቡራዩ ከተማ ጤና ቢሮ በሶስተኛ ደረጃ የዋንጫ ተሸላሚ ሆነዋል።
አቶ ጀግናው ግዛው የቡራዩ ከተማ ከንቲባ በእውቅና አሰጣጥ እና ሽልማቱ ላይ የተገኙ ሲሆን የቡራዩ ከተማን ሰላም እና ብልፅግና ለማረጋገጥ ሴክተር መስሪያ ቤቶች እና ተቋማት በጋራ እና በትብብር መስራት ይጠበቅባቸዋል ያሉ ሲሆን በ2013 የበጀት አመት ከተመዘገበው የእድገት ደረጃ በበለጠ በ2014 ዓ.ም ከተማዋን ከላቀ የእድገት ደረጃ ላይ ለማድረስ ሁላችንም የበኩላችንን እንወጣ ብለዋል።
በ2013 የበጀት አመት በአጠቃላይ የላቀ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ተቋማት በቀጣይ አመት የበለጠ አበርክቶ እንዲኖራቸው ጥሪ ቀርቧል።
(በቁምነገር አህመድ)