የብልፅግና ፓርቲና የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ምክክር አደረጉ

ጥቅምት 18/2014 (ዋልታ) – የብልፅግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) እና በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ጃኦ ዚዩን በብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የሁለቱ ፓርቲዎች ቀጣይ ግንኙነት በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ ምክክር አድርገዋል።

ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ቻይና ለኢትዮጵያ እድገትና ብልፅግና የምታደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ በተለይም በቅርቡ ኢትዮጵያ የገጠማትን የውስጥ ፈተና በራሷ መፍታት እንደምትችል ቻይና የያዘችውን አቋም የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡

የብልፅግና ፓርቲ ከቻይና የብልፅግና ስኬቶች ብዙ ልምዶችን እንዳገኘና ወደፊትም ልምዶችን እንደሚቀስም ማሳወቃቸውን ከብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

የቻይና አምባሳደር ጃኦ ዚዩነ በበኩላቸው የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ምንጊዜም ለኢትዮጵያ እድገትና ብልፅግና ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል ጠቅሰው በቀጣይም መደጋገፍን መሰረት ባደረገ መልኩ ለጋራ ዓላማና ፍላጎት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

አምባሳደሩ የዛሬ 50 ዓመት ቻይና በተባበሩት መንግስታት ከአምስቱ ሃያል ሀገራት እንድትገባ ድምፅ ከሰጡ ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ በመሆኗ ምስጋና አቅርበዋል፡፡