ሰኔ 22/2013 (ዋልታ) – የቦሌ ለሚ እንዱስትሪያል ፓርክ ከ18 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰራተኞች የሥራ እድል መፍጠሩን የፓርኩ ስራ አስኪያጅ ትንሳዔ ይማም ገለጹ፡፡
በፓርኩ ከቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ሥራ እድል ፈጠራ እንዲሁም የውጭ ምንዛሬን የማምጣት እሳቤን ይዞ የተቋቋመ መሆኑን ስራ አስኪያጁ አመላክተዋል::
በ353 ሄክታር መሬት ላይ ግንባታውን ባደረገው ፓርክ ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችን ወደ ውጭ ገበያ በመላክ በተያዘው በጀት አመት 44 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማግኘት እንደተቻለም ተገልጿል፡፡
ፓርኩ በውስጡ በርካታ መሰረተ ልማት የተሟላለት በመሆኑ በቀጣይም የሥራ እድል ፈጠራን ከማጠናከር አኳያ በርካታ ስራዎችን ለመስራት መታቀዱ ተጠቁሟል::
የሰራተኛውን ደህንነት ከመጠበቅ እና የኑሮ ጫናን በመቀነስ እሳቤ በፓርኩ ውስጥ የሚሰሩ ድርጅቶችን በማስተባበር በግቢው ውስጥ የመኖሪያ ቤት ግንባታ እንደተጀመረም ተመልክቷል::
የፓርኩ የስራ እንቅስቃሴ በዛሬው እለት ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ተቋማት በተውጣጡ ጋዜጠኞች ተጎብኝቷል::
(በሄብሮን ዋልታው)