የተባበሩት መንግስታት የዳርፉር ተልዕኮውን እንዲያራዝም አምነስቲ ጠየቀ

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የሱዳን መንግስት ለንጹኃን ዜጎች ጥበቃ ማድረግ ባለመቻሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሱዳን ዳርፉር ያለውን ተልዕኮ ለስድስት ወራት እንዲያራዝም ጠይቋል፡፡

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኑ መንግስት በተቆጣጠረባቸው አካባቢዎች የሱዳን ኃይሎች ለዜጎች ጥበቃ ማድረግ አለመቻላቸውን በመጥቀስ ነው ድርጅቱ ተልዕኮውን እንዲያራዝም ጥያቄ ያቀረበው፡፡

የሱዳን መንግስት ኃይሎች ንጹሃን ዜጎችን ለመጠበቅ ያላቸው ዝግጁነት እንዳሳሰበውም  ገልጿል ፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ዜጎች በአማጺያን ከሚሰነዘሩባቸው ጥቃቶች ለሚያደርገው ጥበቃ አምነስቲ አመስግኗል::

እ.ኤ.አ. ከ2003 ጀምሮ በሱዳን መንግሥት እና በአማጺያን በተደረገ ውጊያ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲሞቱ በሚሊየን የሚቆጠሩ ከቄያያቸው ተፈናቅለዋል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው፡፡