የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ለአፍሪካ ቀንድ አገራት የ85 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገች

የመጋቢት 1/2014 (ዋልታ) የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአፍሪካ ቀንድ አገራት ሰብዓዊ ተግባራት የሚውል የ85 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገች፡፡

በተባበሩት መንግሥታት የሰብኣዊ ጉዳዮች ዋና ጸሐፊ እና የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፍትስ በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ የቀረበው የገንዘብ ድጋፍ በአፍሪካ ቀንድ የተከሰተውን ድርቅ ለመከላከል የሚውል መሆኑን ገልፀዋል።

ድጋፉ ከፋሚን ረሊፍ ፈንድ ጋር በመቀናጀት የቀረበ ሲሆን በተለያዩ ዓለም ዐቀፍ የሰብኣዊ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች አማካኝነት ለየአገራቱ እንደሚከፋፈልም ተገልጿል፡፡

በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ ሻክቦት ቢን ናህያን አል ናህያን አገራቸው ለአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት ትልቅ ቦታ እንደምትሰጥ ተናግረዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ በአካባቢው ላይ እያሳደረ ያለው ተጽዕኖ የሰብኣዊ ሁኔታውን እንዳባባሰው የጠቀሱት ሚኒስትሩ የቀረበው ድጋፍ አፋጣኝ ዕርዳታ የሚሹ አካባቢዎችን በፍጥነት ለመደገፍ እንደሚረዳ መናገራቸውን ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ አመላክቷል።