የተኩስ አቁም ውሳኔው የሰብዓዊ ድጋፍን ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ ዕድል ፈጥሯል – የዓለም ምግብ ፕሮግራም

ሰኔ 10/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ መንግሥት የተላለፈው ሰብዓዊነትን ማዕከል ያደረገ የተኩስ አቁም ውሳኔ በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍን ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ ዕድል መፍጠሩን የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታወቀ።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ባስሊ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን ባጠናቀቁበት ወቅት እንደገለጹት ባለፉት ሁለት ወራት 2 ሺሕ 500 እርዳታ የጫኑ መኪኖች ወደ ትግራይ ገብተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈው መጋቢት ወር ተኩስ አቁም ካወጀ በኋላ ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የክልሉ ነዋሪዎች እርዳታ እየደረሰ መሆኑን አንስተዋል።

ተኩስ አቁሙ በችግር ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን የታደገና በመሆኑ በዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ አድናቆት እንደተቸረውም ነው ያነሱት።

ዋና ዳይሬክተሩ በድርቅ የተጎዳውን የሶማሌ ክልል መጎብኘታቸውን ጠቅሰው ተደጋጋሚ ድርቅ፣ ግጭት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት የኢትዮጵያን የምግብ ዋስትና ችግር አባብሶታል ነው ያሉት።

ዋና ዳይሬክተሩ በድርቅ የተጎዳውን የሶማሌ ክልል መጎብኘታቸውን ጠቅሰው ተደጋጋሚ ድርቅ፣ ግጭት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት የኢትዮጵያን የምግብ ዋስትና ችግር አባብሶታል ነው ያሉት።
በአገሪቷ የተለያዩ ችግሮች በመከሰታቸው በበርካታ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች የእለት ደራሽ ምግብ እንደሚያስፈልጋቸው ጠቅሰው ከዚህ አኳያ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከእርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር አንጻር ቀድሞ ሲያከፋፍል የነበረውን ድጋፍ ለመቀነስ መገደዱን አንስተዋል።
ዓለም ዐቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የጠየቁት።
በኢትዮጵያ ያለው ተደጋጋሚ ድርቅና የአየር ንብረት ለውጥ በርካታ ዜጎች ሰብዓዊ እርዳታ ፈላጊ እንዲሆኑ አድርጓል ያሉት ደግሞ የስዊዲን ዓለም ዐቀፍ ትብብር ሚኒስትር ማቲልዳ ኤርንካራንስ ናቸው።
መንግሥታቸው ኢትዮጵያውያንን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን እና ስዊድን በኢትዮጵያ የምትተገብረውን የአምስት ዓመት የልማት ስትራቴጂ እንዳዘጋጀች መግለጻቻውን ኢዜአ ዘግቧል።
የልማት ስትራቴጂው በየዓመቱ የ35 ሚሊዮን ዶላር በጀት ያለው ድጋፍ እንዳካተተም ጠቁመዋል።