ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት የክልሎች ሁለንተናዊ ድጋፍ ወሳኝነት እንዳለው ተመላከተ

ሰኔ 10/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ሠላማዊ ሁኔታ ለማሸጋገር ተስፋ ለተጣለበት ሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት የክልሎች ሁለንተናዊ ድጋፍ ወሳኝነት እንዳለው ተመላከተ።

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥትና ከባለድርሻ አካት ጋር ዛሬ በአሶሳ ከተማ ውይይት አድርጓል፡፡

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ በዚህ ወቅት እንዳሉት ኮሚሽኑ ኅብረተሰቡ በጉጉት የሚጠብቀውን ሀገራዊ ምክክር ለማስጀመር እየሰራ ነው፡፡

“ሀገራዊ ምክክሩን አካታች ማድረግ ወሳኝ ነው” ያሉት ኮሚሽነሯ ይህንኑ መሰረት በማድረግ ከክልሎች ጋር የትውውቅ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ ስኬት ጠንካራ የቅድመ ዝግጅት ሥራ መስራት አስፈላጊ ነው መሆኑን ያመለከቱት ኮሚሽነር ሂሩት ክልሎች ለኮሚሽኑ የእውቀት፣ የሀሳብ ፣ የበጀት እና ሌለችንም ሁለንተናዊ ድጋፎች እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

ኮሚሽነር መላኩ ገብረማርያም በበኩላቸው ሀገራዊ ምክክር አድርገው ሳይሳካቸው የቀሩ ሀገራት ዋነኛ ችግራቸው ለውይይት አጀንዳ ተቀርጾ ለኅብረተሰቡ በመሰጠቱ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክሩ መሰል ችግር እንዳያገጥመው ኅብረተሰቡ ራሱ የመወያያ ሃሳቦችን በነጻነት እንዲያፈልቅ ለማድረግ ኮሚሽኑ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

በየወረዳው ያለውን ኅብረተሰብ በምክክሩ ለማካተት እንደሚሰራ ጠቁመው በቅርቡ የምክክሩን ጉዳይ የሚከታተሉ የኮሚሽኑ ሰራተኞች በየክልሉ ይመደባሉ ብለዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው ኮሚሽኑ የያዘው ዓላማ ኢትዮጵያዊያንን የጋራ አሸናፊ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።
ምክክሩ ሀገራዊ መግባባት የማምጣት አቅም እንዳለው አመልክተው የክልሉ መንግሥት ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡
በውይይቱ የተሳተፉት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሀገር ሽማግሌዎች በበኩላቸው ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት ባህላዊ እሴቶችን መጠቀም እንደሚገባ እና የጋራ ተጠቃሚነትን ማስቀደም እንደሚያስፈልግ መናራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።