የተጀመረውን የሰላም ጅማሮ በመተግበር ለውጤታማነቱ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ሚያዝያ 15/2015 (ዋልታ) ሁላችንም ህዝቦችን በማቀራረብ እና የፈረሱ የአብሮነት ድልድዮችን በመገንባት የተጀመረውን የሰላም ጅማሮ በመተግበር ለውጤታማነቱ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

“ጦርነት ይብቃ ሰላምን እናጽና” በሚል በትላንተናው ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ ወዳጅነት አደባባይ የምስጋና እና የዕውቅና ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት አሰቃቂው የጦርነት ወቅት አልፎ የሰላም ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል።

ለአፍሪካዊያን ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ ማምጣት እንደሚቻል ሀገራችን ለዓለም ምስክር ሆናለች ያሉት ከንቲባዋ ነገር ግን ጦርነት ማብቃቱ ብቻ ለሰላም መስፈን ዋስትና ስለማይሆን ሁላችንም ህዝቦችን በማቀራረብ እና የፈረሱ የአብሮነት ድልድዮችን በመገንባት የተጀመረውን የሰላም ጅማሮ  በመተግበር ለዉጤታማነቱ ሀላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

ለኢትዮጵያችን ሰላምን በመሻት ለተደረገው ስምምነት መተግበር የተረባረባችሁ ወዳጆቻችን ምስጋና ይገባቹሃል ሲሉም አክለዋል፡፡