የተጀመረው የህግ የበላይነትን የማስፈን ሥራ በሽብር ቡድኖች ሴራ በፍጹም አይደናቀፍም – የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት

ሰኔ 13/2014 (ዋልታ) መንግሥት የጀመረው የህግ የበላይነትን የማስፈን ሥራ በሽብር ቡድኖች ሴራ በፍጹም አይደናቀፍም ሲል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

አገልግሎቱ ባወጣው መግለጫ መንግሥት በመላ ሃገሪቱ ሰላምን ለማስፈን የኢመደበኛ ታጣቂዎችንና በሽብር ቡድንነት የተፈረጁ ቡድኖችን እንቅስቃሴ ለመግታት ሁሉን አቀፍ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁሟል።

ይህ የመንግሥትና የመላው ጸጥታ ኃይሎች የህግ የበላይነትን የማስከበር ተልእኮ ያነጣጠረበት የሸኔ የሽብር ቡድን እየደረሰበት የሚገኘውን ከፍተኛ ሽንፈት ለመሸፈን የጥፋት በትሩን ወደ ንጹሃን አዙሯል ነው ያለው አገልግሎቱ በመግለጫው።

የሽብር ቡድኑ በቅርቡ በጋምቤላ፣ በደምቢዶሎና በጊምቢ ከተሞች ላይ የሰነዘራቸው የሽብር ጥቃቶች በጸጥታ ኃይሉ ቅንጅት ሲከሽፍ በበቀል የሽብር ተግባሩ በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ በርካታ ንጹሃንን ህይወት በግፍ ቀጥፏል፣ ንብረትንም አውድሟል ነው ያለው መግለጫው።

በሽብር ጥቃቱ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖችና ለደረሰው ጉዳት መንግሥት የተሰማውን ልባዊ ሃዘን ይገልጻል ያለው መግለጫው ይህ ቡድን በንጹሃን ላይ የሚያደርሰው ጉዳት የቡድኑን ትክክለኛ ማንነት የሚያሳይ በመሆኑ የጥፋት ኃይሉ ሙሉ በሙሉ እንዲደመሰስ በመላው የክልልና የፌዴራል የጸጥታ ኃይሎች የተጀመረው የተቀናጀ ተልእኮ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብሏል።